የሚድሮክ ወርቅ ማእድን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ለሚያስገነባው የወርቅ ፋብሪካ የግንባታ መሳሪያዎችን ማግኘት የሚያስችለውን ስምምነት ከሴምቴክ ጂኤምቢኤች ኩባንያ ጋር ተፈራረመ።
ስምምነቱን የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የማዕድን ዘርፍ ም/ዋና ስራ አስፈጻሚ ዱላ መኮንን እና የሴምቴክ ጂኤምቢኤች ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ቶማስ ፕሎክበርገር ተፈራርመዋል።
በስምምነቱ መሰረት ሴምቴክ ጂኤምቢኤች ኩባንያ በአመት 1 ሚሊዮን 250 ሺህ ቶን ወርቅ አዘል ድንጋይ ማጣራት የሚችል የወርቅ ፋብሪካ ማሺን የማምረትና የመገንባት ተግባር ያከናውናል።
በተጨማሪም ሴምቴክ ጂኤምቢኤች ኩባንያ ለፋብሪካው የሚያስፈልጉ ምርቶችን በአንድ አመት ውስጥ በማጠናቀቅ ለሚድሮክ መተከል ወርቅ ፋብሪካ እንደሚያስረክብ ሚድሮክ ገልጿል።
ከሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ጋር ስምምነቱን የፈጸመው የሴምቴክ ኩባንያ በፈረንጆቹ 1990 የተመሰረተና መቀመጫውን በኦስትሪያ ኤንስ ከተማ ያደረገ በኢንዱስትሪ፣በሲሚንቶና በማእድን ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ኩባንያ እንደሆነ ይነገራል።
መረጃው ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የተገኘ ነው።
