በሳዑዲ አረቢያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ በሀገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ያልተረጋገጡ መረጃዎችን በማህበራዊ ሚዲያ ከማሰራጨት እንዲቆጠቡ አሳሰበ፡፡
ኤምባሲው ይህን ማሳሰቢያ የሰጠው በሳዑዲ ገጠራማና በረሃማ ቦታዎች በኢትዮጵያዊያን መካከል በቅርቡ በተካሄደ የቡድን ጸብ እና ግጭት ጋር በተያያዘ የግድያ ወንጀል የፈጸመ ግለሰብ ከአምስት ግብረ አበሮቹ ጋር በቁጥጥር ሥር መዋሉን በገለጸበት መግለጫው ላይ ነው፡፡
ይህን የኢትዮጵያውያንን እሴት የማይወክል አፀያፊ ተግባር በቅርበት ሲከታተል መቆየቱን የገለጸው ኢምባሲው ጉዳዩን በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ሲያራግቡ የነበሩ ከ100 በላይ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉም አስታውቋል።
ከሳውዲ አረቢያ የፀጥታ ተቋማት ጋር በመተባበር ወንጀለኞቹ ለፍርድ እንዲቀርቡና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ የጠቀሰው ኢምባሲው በወንጀል የተሳተፉ ግለሰቦችን በተመለከተ ማንኛውም መረጃ ያለው አካል፣ እንዲያሳውቅም ጥሪ አቅርቧል።
