የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን የተለየ የቤት መግዣ ብድር መልሶ ማጠናከሪያ ኩባንያ ለማቋቋም የሚያስችለውን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ተፈራረሙ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት ስምምነቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ፈርመውታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለየ የቤት መግዣ ብድር መልሶ ማጠናከሪያ ኩባንያ በ100 ቢሊየን ብር ካፒታል የተቋቋመ መሆኑን እና የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን 200 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ አስተዋፅኦ የሚያደርግበት ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አዲሱ ኩባንያ በባንክ ዘርፉ ውስጥ ያለውን የጥሬ ገንዘብ ፍሰት አለመመጣጠንን የሚቀርፍ እና በመላው ኢትዮጵያ ተደራሽ የሚሆን የቤት መግዣ ብድር ፋይናንስን እንደሚያስገኝ ተናግረዋል።
ይህ አጋርነት በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገነቡ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶችን ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።መረጃው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የማህበራዊ የትስስር ገፅ የተገኘ ነው።
