አዲስ አበባ ከተማ የአየር ንብረት አደጋዎችን በመቋቋም በዓለም 2ኛ ደረጃ መያዟ ተነገረ።
ይህ የተነገረው ዓለም አቀፉ የጂኦስፓሻል አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ተቋም (አልፋጂኦ) የዓለም ታላላቅ 72 ከተሞችን የአየር ንብረት አደጋ የመቋቋም አቅም ደረጃ ይፋ ባደረገበት ሪፖርቱ ነው።
በዚህ አዲሱ ዓለም አቀፍ ደረጃ መሠረት አዲስ አበባ ከዓለም አቀፍ ከተሞች በ2ኛ ደረጃ እና ከአፍሪካ 1ኛ ደረጃ መያዟ ነው የተነገረው።
ጥናቱ የከተሞችን ዝግጁነት የለካው ከተፈጥሮ አደጋዎች ተጋላጭነት ነጻ በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን አደጋዎችን የመከላከል፣ የማላመድ እና የመቋቋም አቅማቸውን መሠረት በማድረግ ነው።
በዚህ መሠረት የአሜሪካዋ ቺካጎ ከተማ በ1ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ፣ አዲስ አበባ ደግሞ እንደ ሜልቦርን፣ ባርሴሎና እና ፓሪስ ያሉ ታላላቅ የዓለም ከተሞችን በልጣ በዓለም 2ኛ ደረጃ መያዟን የዘኒዮርክ ታይምስ ዘገባ ያሳያል።
ጥናቱ እንደሚያመላክተው፣ ብዙኃኑ የደቡብ እስያ ከተሞች ለአየር ንብረት አደጋ ከፍተኛ ተጋላጭ ሆነው ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ሰፍረዋል።
