የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጳጉሜን 4 – የኅብር ቀንን በማስመልከት በክፍለ ከተሞች፣ ወረዳዎች እና በማዕከል ደረጃ የማዕድ ማጋራት መርሃግብር አካሂደዋል፡፡
ከንቲባዋ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት ማዕድ ማጋራቱ ጧሪ እና ደጋፊ ለሌላቸው፣ ለማኅበራዊ ችግር ለተጋለጡ፣ ለአረጋውያን እና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሠራተኞች የተደረገ የፍቅር ሥጦታ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ ድርጊትም አብሮነትን፣ መረዳዳትንና ሰው ተኮር ተግባራትን ባህል በማድረግ ማኅበራዊ ትሥሥርን ለማጠናከር ያለመ መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ ማዕድ ማጋራት ምግብን ከመመገብ ባለፈ አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ፍቅርን፣ አብሮነትን እና አክብሮትን ለከተማዋ ነዋሪ ማካፈል ጭምር መሆኑን ነው የገለጹት።
ካላቸው ላይ ቀንሰው በከተማዋ ለተካሄደው የማዕድ ማጋራት ፕሮግራም አስተዋጽኦ ላደረጉ ባለሃብቶች፣ ማኅበራት እና ግለሰቦች ምስጋና ያቀረቡት ከንቲባዋ አዲሱ ዓመትም የፍቅር፣ የሰላም እና በትጋት ሰርቶ የመለወጥ ዘመን እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።
