EthiopiaNews

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2019 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ መጀመሩን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሁሉም የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች የ2019 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራ በዛሬው እለት መጀመሩን ባደረኩት ምልከታ አረጋግጫለሁ ያለው ቢሮው ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች በ2019 ዓ.ም ትምህርታቸውን ለመከታተል መመዝገባቸውን ገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሳምሶን መለሰ በአዲሱ የትምህርት አመት ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የተማሪዎችን ውጤትና እና ሥነ ምግባር ለማላቅ በቂ የቅድመ ዝግጅት ስራ መስራቱን አመላክተዋል።

ምክትል ቢሮ ኃላፊው አያይዘውም በትምህርት ዘመኑ ለተማሪዎች በቂ የደንብ ልብሶችን ጨምሮ ደብተሮችና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁሶች ዝግጁ ከመደረጋቸው ባሻገር የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ጥራቱን ጠብቆ ለተማሪዎች ተደራሽ እንዲሆን ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው፤ የትምህርት አመቱ ፍጹም ሰላማዊና ተማሪዎች ውጤታማ የሚሆኑበት አመት እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካል ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።