ማንኛውም ታክስ ከፋይ ለገዢ ባልሰጠው በእያንዳንዱ ደረሰኝ አንድ መቶ ሺህ ብር እንደሚቀጣ የገቢዎች ሚኒስቴር አስጠንቅቋል።
ይህ ቅጣት በታክስ ይግባኝ ባለሥልጣን ሊነሳ አይችልም ያለው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተሻሻለው የታክስ አስተዳደር አዋጅ መሰረት ደረሰኝ አለመቁረጥ የታክስ ደረሰኝ ያለመስጠትን ተጠያቂነት እንደሚያስከትልም አሳስቧል።
ለአንድ ግብይት በተሰጠ ተመሳሳይ ደረሰኝ ላይ የተለያዩ ዋጋዎችን በመመዝገብ የሽያጭ ዋጋን በማሳነስ ደረሰኝ የሰጠ ማንኛውም ሰው በተመሳሳይ የአንድ መቶ ሺህ ብር ቅጣት እንደሚጠብቀው አስገንዝቧል።
እንዲሁም ከገንዘብ መቀጫው በተጨማሪ ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣም ነው የገለጸው።
