የግብፅ የውሃ ሀብትና መስኖ ሚኒስትር ሃኒ ሰዊላም ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት እጅግ ማዘኑን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለፀ።
ሚኒስቴሩ ይሄን ያለው የግብፅ የውሃ ሀብትና መስኖ ሚኒስትር በቅርቡ ኢትዮጵያውያን ትምህርት የላቸውም የሚል አስተያየት መስጠታቸውን ተከትሎ በሰጠው መግለጫ ነው።
ይህ የሚኒስትሩ ንግግር ግብጽ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ባላት ግንኙነት የምትከተለውን ኋላቀር የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ያንፀባረቀ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
በካይሮ እይታ፣ የናይል ተፋሰስ ሀገራት የተፈጥሮ ሀብታቸውን ለመጠቀም ከእሷ ይሁነታ ማግኘት እንደ ግዴታ እንደሚቆጠር ያስታወሰው ሚኒስቴሩ ይህ ግን ግብፅ ማንኛውንም የላይኛው የተፋሰስ ሀገራትን ሳታማክር የአስዋን ግድብን ከገነባችበት እውነታ ጋር በእጅጉ የሚቃረን መሆኑን አብራርቷል።
ሚኒስቴሩ በግብፅ ባለስልጣናት የሚሰነዘሩ አላስፈላጊ ውጥረትን የሚቀሰቅሱ አስተያየቶችና የሚያንጸባርቁት አቋም ኢፍትሐዊ መሆኑን ገልፆ፤ ኢትዮጵያ ዓባይን ጨምሮ የተፈጥሮ ሀብቶቿን የመጠቀም ሉአላዊ መብቷን አጥብቃ ታረጋግጣለችም ብሏል፡፡
ሚኒስቴሩ የሀገራትን የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም ሉአላዊ መብት የሚነፍግ ማንኛውንም የውሃ የበላይነት አስተሳሰብን ኢትዮጵያ አጥብቃ እንደምትቃወም ገልጿል።
