EthiopiaNews

በኢትዮጵያ ያለው የስራ አጥነት ምጣኔ 9 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ገለጸ፡፡

አገልግሎቱ ከ2016 እስከ 2017 ዓ.ም መጨረሻ ያካሄደውን የስራ አጥነት ምጣኔ ከሰሞኑ ይፋ ባደረገበት ሪፖርቱ በኢትዮጵያ ያለው የስራ አጥነት ቁጥር እየጨመረ መሄዱን አሳይቷል፡፡

ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ስራ አጥ መሆናቸው ያመለከተው ጥናቱ በተለይ የወጣቶች ስራ አጥነት ደግሞ 12 ነጥብ 9 በመቶ መድረሱን፣ ከፆታ አንፃር ሲታይ ደግሞ ከስራ አጦቹ መካከል የሴቶቹ ቁጥር ከወንዶቹ የበለጠ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን በከተሞች ያለው የስራ አጥነት ምጣኔ ከገጠሩ በእጥፍ የበለጠ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት መጨመሩ እና ከተሞችም ስራ የመፍጠር አቅማቸው ዝቅተኛ መሆኑን የጠቀሰው ጥናቱ የገጠሩ ክፍል የስራ አጥነት ምጣኔ 10 ነጥብ 2 በመቶ እንዲሁም በከተሞች ያለው 20 ነጥብ 6 በመቶ መሆኑን አሳይቷል፡፡

ከፍተኛ የስራ አጥነት ችግር ከታየባቸው መካከል አዲስ አበባ 19 ነጥብ 1 በመቶ በማስመዝገብ ቀዳሚ ስትሆን፣ ድሬዳዋ 14 ነጥብ 5 በመቶ፣ ትግራይ ክልል 12 በመቶ፣ ኦሮሚያ ክልል 10 ነጥብ 5 በመቶ እንዲሁም በአማራ ክልል 9 ነጥብ 2 በመቶ መመዝገቡ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ደግሞ ዝቅተኛው 5 ነጥብ 6 በመቶ የስራ አጥነት ምጣኔ ያላት ክልል መሆኗን ጥናቱ አመልክቷል፡፡

በተጨማሪም የኢንዱስትሪው ዘርፍ እየፈጠረ ያለው የስራ እድል አዝጋሚ መሆኑን ያሳየው ጥናቱ በተመሳሳይ የግብርናው ዘርፍ ደግሞ ቅናሽ ማሳየቱንና በአንጻሩ የአገልግሎት ዘርፉ የተሻለ እድገት ማሳየቱም ተገልጿል፡፡

በአገራዊ ደረጃ አጠቃላይ ከተሰማራው የሰው ኃይል ውስጥ መደበኛ ስራተኛው 53 ነጥብ 9 በመቶ እንደሚይዝና መደበኛ ያልሆነ ስራ ደግሞ 44 ነጥብ 2 በመቶ የሚሆነውን የሰው ኃይል እንደሚሸፍን በጥናቱ ሰፍሯል።