የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በ81ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን ከአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ጋርሺያ ጋር መወያየታቸው ተነገረ።
ሁለቱ ወገኖች በጋራ ፍላጎቶች እንዲሁም በቀጣናዊ ሰላም እና ደኀንነት ጉዳዮች ላይ የተወያዩ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለውን የንግድ እና ኢኮኖሚ ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እና አሜሪካ በግንቦት ወር 2018 ዓ.ም በዋሺንግተን ዲሲ በሦስት ዋና ዋና ዘርፎች ማለትም በኢኮኖሚ እድገት፣ ንግድና ኢንቨስትመንት፤ በደኀንነትና መከላከያ ትብብር፤ እንዲሁም በቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋት ዙሪያ ያተኮረ የሁለትዮሽ ውይይት ማካሄዳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውሷል።
የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ጋርሺያ ከ16 ቀናት በፊት በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
አቶ ጌታቸው ረዳ ከተ.መ.ድ. የፖለቲካ እና ሰላም ግንባታ ጉዳዮች ረዳት ዋና ፀሐፊ ጋር መምከራቸው ነው የተነገረው።
አማካሪው ኢትዮጵያ በሱዳንም ሆነ በአጠቃላይ በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሚደረጉ ጥረቶችን ለመደገፍ ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
መረጃው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘ ነው።
