የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የመንግሥት ምስረታና የምክር ቤቱ መክፈቻ መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም እንደሚከናወን አስታወቀ።
ምክር ቤቱ ይሄን ያለው የመንግሥት ምስረታና የምክር ቤቱ መክፈቻ ስነ ስርዓት በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ነው።
በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 50 ንዑስ አንቀጽ 3 መሠረት የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት መሆኑንና ተጠሪነቱም ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሆነ ያስታወሱት የም/ቤቱ አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ የምክር ቤቱ የሥራ ዘመንም በመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ እንደሚጀምር በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 58 ንዑስ አንቀጽ 2 መደንገጉን አንስተዋል፡፡
እንደዚሁም በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 56 መሠረት በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅቶች የፌዴራሉን መንግሥት የሕግ አስፈጻሚ አካል እንደሚያደራጅና እንደሚመራ ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም መሠረት የዓመቱ የመንግሥት ምስረታ እና የምክር ቤቱ መክፈቻ ሥነ-ስርዓት መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም እንደሚከናወንና ለዚህም አስፈላጊው ዝግጅት ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን አፈ ጉባኤው ገልፀዋል።
አፈ-ጉባኤው በምርጫው በሕዝብ ድምፅ የተመረጠው መንግሥት ቀጣዩን አምስት ዓመታት ሀገርና ሕዝብ የመምራት ኃላፊነት የሚረከብ መሆኑን ተናግረዋል።
