EthiopiaNews

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ የጭነት አገልግሎት ዘርፍ ያለውን ተወዳዳሪነት ለማስቀጠል 10 የቦይንግ 777 የጭነት አውሮፕላኖችን ለመግዛት የግዥ ስምምነት መፈጸሙን አስታወቀ።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው እና የቦይንግ ኩባንያ የዓለም አቀፍ የንግድ ሽያጭና ማርኬቲንግ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት ብራድ ማክሙለን ሲፈራረሙ ከ10 ዘመናዊ አውሮፕላኖች ውስጥ ስምንቱ ከፍተኛ አቅም ያላቸው የጭነት አውሮፕላኖች መሆናቸው ስምምነቱን ለየት ያደርገዋል ተብሏል።

ይህ ግዢ የአየር መንገዱን የዓለም አቀፍ የጭነት ገበያ የበላይነት በከፍተኛ ደረጃ ለማጠናከር እና የወደፊት የዕድገት ጉዞውን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረውም ተገልጿል።

የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ አየር መንገዱ ከቦይንግ ጋር ያለው የጠበቀ ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰው፤ ይህ ግዢ የጭነት አገልግሎቱን ከማዘመን ባለፈ የአውሮፕላኖቹን ቁጥር በማሳደግ የተቋሙን አቅም ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ተናግረዋል።