EthiopiaNews

በትግራይ ክልል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን በአቅራቢያቸው ለሚገኝ የመከላከያ ሠራዊት በማስረከብ ወደ ተሃድሶ ማዕከል እንዲገቡ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ጥሪ አቅርቧል፡፡

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ ኮሚሽኑ ከህዳር 2017 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ በማቋቋም ወደ መደበኛ ሕይወት እንዲመለሱ ማድረጉን ገልጸዋል።

መንግስት በትግራይ ክልል ከፍተኛ ሃብት በመመደብ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም የተለያዩ ተግባራትን ቢያከናውንም የሕወሓት ቡድን የፕሪቶሪያው ስምምነትን በማፍረስ ወደ ተሃድሶ ማዕከል ለመግባት ፈቃደኛ የነበሩ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና እንዳይወስዱ ሲያደናቅፍ መቆየቱን ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ሆኖም የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ለሚመጡ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት ወደ መደበኛ ሕይወት ለማስገባት መንግስት አሁንም በሩ ክፍት መሆኑን ያረጋገጡ ሲሆን በትግራይ ክልል የቀደሞ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን በአቅራቢያቸው ለሚገኝ የመከላከያ ሠራዊት እያስረከቡ ወደ ተሃድሶ ማዕከል እንዲገቡም ጥሪ አቅርበዋል።