የአለም ባንክ በፈረንጆቹ 2026 ለኢትዮጵያ አውጥቶት የነበረውን የ8 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ትንበያን ወደ 9 ነጥብ 2 በመቶ ከፍ አደረገ።
ባንኩ ባወጣው አዲስ ሪፖርት በተመሳሳይ ከ7 ወራት በፊት ለአፍሪካ ሃገራት አውጥቶት የነበረውን የ2026 ዓመት የ4 ነጥብ 1 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ትንበያን ወደ 4 ነጥብ 3 በመቶ አሳድጓል።
ኢትዮጵያ፣ ዛምቢያ፣ ናይጄሪያ እና አንጎላ ለአመታት እያካሄዱት ባለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሳቢያ ዘንድሮ የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት ያስመዘግባሉ ያለው ባንኩ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሃገራት የኢኮኖሚ እድገት ትንበያ ላይ ማሻሻያ የተደረገው የሃገራቱ የኢኮኖሚ አፈፃፀም አበረታች በመሆኑ ነው ብሏል።
የአፍሪካ ሃገራት የኢራን ጦርነት ያስከተለው የነዳጅ ዋጋ መጨመር እና የአቅርቦት ሰንሰለት ችግሮችን መቋቋም እንደቻሉ ባንኩ ገልጿል።
ርዕሰ ብሔር ታዬ አፅቀ ስላሴ ዘንድሮ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ10 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ያስመዘግባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ትናንት በህዝብ እንደራሴዎችና በፌደሬሽን ምክር ቤት የጋራ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር መግለፃቸው ይታወሳል።
