ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ከገንዘብ ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር ያለውን የትብብር አድማስ ማስፋት እንደሚፈልግ አስታወቀ።
ይህ የተባለው የ2026 የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ በታይላንድ ባንኮክ እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ከስብሰባው ጎን ለጎን ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የፊሲካል ጉዳዮች ክፍል እና ከገንዘብና ካፒታል ገበያዎች የስራ ክፍል ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን አድርጓል።
በውይይቱ አይኤምኤፍ ለገንዘብ ሚኒስቴር እየሰጠ የሚገኘው የቴክኒክ ድጋፍ አፈጻጸም የተገመገመ ሲሆን በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሪፎርም አጀንዳዎች መሠረት በቀጣይ ተጨማሪ ድጋፍ የሚደረግባቸውን ዕድሎችና የትብብር መስኮች ላይ ምክክር ተደርጓልም ነው የተባለው።
ውይይቱ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በኩል ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እየተደረገ ያለውን የቴክኒክ ድጋፍም ያካተተ ስለመሆኑ ተገልጿል።
የተቋሙን የማስፈጸም አቅም የበለጠ ለማጠናከርና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የጀመረውን የሪፎርም አጀንዳ ለማጠናከር የሚያስችሉ ተጨማሪ የድጋፍ መስኮችን የመለየት ሥራም መከናወኑነ ሰምተናል፡፡
