የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከክልል ጤና ቢሮዎች እና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር የኢቦላ በሽታ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባና ቢከሰትም በፍጥነት ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅነት ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አስታወቀ።
የኢቦላ በሽታ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በአሁኑ ወቅት ደግሞ በኬንያ መከሰቱን ተከትሎ፣ በሸታው ወደ ሃገር ቤት እንዳይገባ በአየርና በየብስ መግቢያ እና መውጫ በሮች ላይ የጤና ቅኝትና ቁጥጥር እየተካሄደ መሆኑንም ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
በሽታው ከተከሰተባቸው ሀገሮች ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገቡ ሰዎች ሳምንቱን ሙሉ ቅኝት፣ መለየት እና ክትትል እየተካሄደ እንደሚገኝ የገለጸው ሚኒስቴሩ የላቦራቶሪ ምርመራ አቅምን የማጠናከር፣ የመለየት እና ፈጣን ምላሽ ሰጭ ቡድኖችን የማደራጀት ሥራዎችም እየተከናወኑ ይገኛል ተብሏል።
ሚኒስቴሩ ሕብረተሰቡ በበሽታው ዙሪያ የሚሰጡ መረጃዎችን እንዲከታተል፣ የበሽታው ወረርሽኝ ከተከሰተባቸው ሀገራት የሚመጡ ወይም ለበሽታው ተጋላጭ ከነበሩ ሰዎች ጋር ንክኪ የነበራቸው ሰዎች ትኩሳት፣ የጡንቻ ሕመም፣ ማስታወክ ወይም ያልተለመደ የደም መፍሰስ ምልክቶች ከታዩባቸው ወዲያውኑ ለጤና ተቋም በማሳወቅ የጤና ምርመራና ክትትል እንዲያደርጉ ጥሪውን አስተላልፏል።
