EthiopiaNews

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ስም ከሚፈጸም ማጭበርበር ዜጐች እራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳሰበ።

ሚኒስቴሩ ይሄን ያለው ሐሰተኛ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ማስታወቂያዎች በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ነው።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርን ስም፣ አርማ፣ የከፍተኛ አመራሮችን ፎቶና ፊርማ በመጠቀም ሐሰተኛ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ማስታወቂያዎች በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገፆች እየተሰራጩ እንደሚገኙ ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከዘረጋው ሕጋዊ ስርዓት ውጪ ለየትኛውም አካል የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪትን ውክልና የሰጣቸው ተቋማትም ሆኑ ግለሰቦች የሉም ብሏል።

ሕብረተሰቡ በእነዚህ አሳሳች ማስታወቂያዎች ተታልሎ ለአላስፈላጊ ወጪና እንግልት እንዳይዳረግ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ሚኒስቴሩ አሳስቧል።

እነዚህ ማስታወቂያዎች በተለያዩ ሀገራት የሥራ ዕድል እንደሚያመቻቹ የሚገልፁ፣ ሂደቱን ለማስጨረስ ቀስ በቀስ ገንዘብ የሚጠይቁና ገንዘብ ከተቀበሉ በኋላ አድራሻቸውን የሚያጠፉ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
መረጃው ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የተገኘ ነው።