የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ህገ ወጥ የይለፍ ወረቀት በሚጠቀሙ አሽከርካሪዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚያደርግ አስጠነቀቀ፡፡
በከተማዋ ለሚከናወኑ ኩነቶች እንደ አስፈላጊነቱ ዕውቅናና የይለፍ ማረጋገጫ እንደሚሰጥ ያስታወቀው ቢሮው ነገር ግን ባደረገው ክትትልና ቁጥጥር ያልተፈቀደላቸው አካላት ህገ ወጥ የይለፍ ወረቀት በመያዝ እያጭበረበሩ መሆኑን ደርሼበታለሁ ብሏል።
ህገ ወጦቹ የትራፊክ ቁጥጥርን በመጣስ፣ ከመጠን በላይ በፍጥነት በማሽከርከር፣ ከተፈቀደው መስመር በተቃራኒ በመንዳት፣ የመኪና መለያዎችን ያለ አግባብ በመጠቀም፣ የጥቁር መስታወት ሽፋኖችንና የVIP ፈቃዶችን ያለ ሕጋዊነት መጠቀምና መሰል የህግ ጥሰቶችን እየፈጸሙ በመሆኑ ይህን ተግባር ለማስቆም እየሰራ መሆኑንም ገልጿል፡፡
የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ብሎም ወንጀለኞችን ለህግ በማቅረብ አስተማሪ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ የገለጸው ቢሮው የከተማዋ ነዋሪዎች መሠል ህገ ወጥ ተግባር የሚፈፅሙ አካላትን ሲመለከቱ ለጸጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጡም መልዕክቱን አስተላልፏል።
