EthiopiaNews

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ138 ሺህ በላይ አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረጉን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጌቱ ገረመው አስታወቁ።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንዳስታወቁት፣ በሩብ ዓመቱ የተመዘገበው ውጤት ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ29 በመቶ በላይ ዕድገት አሳይቷል።

የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ከሆኑ አዳዲስ ደንበኞች መካከል 123 ሺህ 509 የሚሆኑት የቅድመ ክፍያ 15 ሺህ 227 ደግሞ የድህረ ክፍያ ሥርዓት ተጠቃሚዎች መሆናቸውንም ዋና ስራ አስፈጻሚው አክለው ተናግረዋል።

አዳዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ በተከናወነው ሥራ፣ ከዋናው የኤሌክትሪክ ግሪድ 21፣ ከኦፍግሪድ ደግሞ 9፣ በድምሩ 30 ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡

ለነባር ደንበኞች አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ለማረጋገጥ 630 ኪ.ሜ የዲስትሪቢዩሽን ኔትወርክ መልሶ ግንባታ እንዲሁም 275 የዲስትሪቢዩሽን ትራንስፎርመሮችን የማሻሻል ሥራ መከናወኑንም ገልጸዋል።