የከተማ አስተዳደሩ የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 03 ያልተጣራ ፍሳሽ ወደ ወንዝ የለቀቁ 2 የመኪና እጥበት ድርጅቶች 800 መቶ ሺህ ብር በመቅጣት አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ፡፡
ድርጅቶቹ ከመኪና እጥበት የሚወጣውን ያልተጣራ ፍሳሽ ቆሻሻ በቀጥታ ወደ መስመር ቱቦና ወደ ወንዝ በማገናኘት የአካባቢ ብክለት ሲፈጽሙ በመገኘታቸው ቅጣቱ እንደተጣለባቸው ነው ባለስልጣን መ/ቤቱ ያስታወቀው።
በዚህም መሠረት ሚሊኒየም ዘመናዊ የመኪና እና ምንጣፎች እጥበት (አራት መቶ ሺህ) ብር እንዲሁም ዎሽ ካር 24 አወርስ የመኪና እጥበት (አራት መቶ ሺህ) ብር ተቀጥተዋል።
ድርጅቶቹ በድምሩ (ስምንት መቶ ሺህ) ብር ቅጣት የተጣለባቸው ሲሆን ወደ ወንዝ እና መስመር ቱቦ ተያይዞ የነበረው ህገ-ወጥ ፈሳሽ ማስተላለፊያ መስመር ወዲያውኑ እንዲቋረጥ ተደርጓል።
ባለሥልጣኑ ማንኛውም የግልም ሆነ የመንግሥት ተቋም የአካባቢን ንጽህና የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበት በማሳሰብ መሰል ህገ-ወጥ ድርጊቶችን በሚፈጽሙ አካላት ላይ የሚወሰደው አስተዳደራዊ እና ሕጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
መረጃው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን የተገኘ ነው።
