ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጎንደር የሚገኘውን የመገጭ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት አስመረቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ፕሮጀክት ረጅም ዓመታት የዕቅድና አተገባበር መጓተት ቢፈታተነውም፣ የአፈጻጸም ችግሮቹን በመፍታት ወደ ታላቅ በረከት መለወጥ ችለናል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ግድብ 185 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ የመያዝ አቅም ያለውና ከ17 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በመስኖ በማልማት በአካባቢው የሚኖሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን በቀጥታ ተጠቃሚ በማድረግ የአካባቢውን ነዋሪዎች የልማት ጥያቄ በዘላቂነት መመለስ የሚያስችል ታላቅ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
ግድቡ ለጎንደር ከተማና በዙሪያዋ ላሉ ከተሞች አስተማማኝ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ከማቅረብ ባለፈ፣ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ መነቃቃትን ይዞ የመጣ መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለፁት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግድቡ ሰው-ሰራሽ ሀይቅ ዙሪያ የሚስፋፉት የከተማ ግብርና፣ መጠነ-ሰፊ የአሳ እርባታ፣ እንዲሁም ለቱሪዝም ልማት የሚሆኑ የመዝናኛ ሪዞርቶች እና ሎጆች ለአካባቢው ወጣቶች ሰፊ የስራ ዕድል የሚፈጥሩና የንግድ እንቅስቃሴውን የሚያሳድጉ ናቸው ብለዋል።
ይህን ስኬት ለእይታ ለማብቃት በጥብቅ ክትትልና ድጋፍ እውን ማድረግ መቻሉን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎንደር ገና ብዙ ሊሰራላት የሚገባ ከተማ እንደመሆኗ ህዝቡ በልማቱ ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ እድገት ሁሉንም አካባቢዎች ያካተተና ሁሉንም ዜጋ እኩል የሚያቅፍ እንዲሆን በትጋት እንስራለን ብለዋል።
