EthiopiaNews

በመዲናዋ ንግድ ፈቃድ ሳያወጡና ደረሰኝ ሳይለዩ ለሽያጭ የቀረቡ 45 መኪኖች ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱ ተገለፀፎቶ)web

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ቂርቆስ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት በመዲናዋ ለሚከናወን የመኪና ሽያጭ የከተማው ንግድ ፈቃድ ሳያወጡና ደረሰኝ ሳይለዩ ለሽያጭ የቀረቡ 45 መኪኖች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ፡፡

ቢሮው ይሄን ያለው ከመኪና አስመጪዎች ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ የግብር ስወራ እና የታክስ ማጭበርበር ወንጀሎች ለመከላከል እየወሰደ ያለውን አስተዳደራዊ እርምጃ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ነው።

የቂርቆስ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የህግ ተገዢነት ምክትል ስራ አስኪያጅ ሄኖክ ዘውዴ አንዳንድ መኪና አስመጪዎች ተሽከርካሪዎችን ከመሸጫዎች አውጥተው በየመንደሩ፣ በመጋዘኖች እና በሃይማኖት ተቋማት ግቢ ውስጥ በመደበቅና በማቆም በህገ-ወጥ መንገድ ሽያጭ እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ቅርንጫፍ ፅ/ቤቱ ባካሄደው የቁጥጥር ስራ በመዲናዋ ለተሸጠ ሽያጭ ለገዢ ሊሰጥ የተገባ የአዲስ አበባ ደረሰኝ ሳይለዩ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ የተገኙ ከ45 በላይ መኪኖች ላይ ተገቢውን የህግ ማስከበር ስራ መስራቱን ገልጸዋል።

አሁንም ወደ ህጋዊ ስርአት ባልገቡት ላይ የሚስተዋለውን ህገወጥ የግብር ስወራ ለመከላከል የተጠናከረ ቁጥጥርና እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ ቢሮው ገልጿል፡፡

በከተማዋ ውስጥ በህጋዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ የንግድ ፈቃድ ማውጣት ወይም የክልል ንግድ ፈቃድን በከተማው ማስጠቀስ፣ ደረሰኝ መለየት እንዲሁም በመመሪያ ቁጥር 166/2014 መሰረት ዓመታዊ ግብርን ለሚመለከተው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በአግባቡ መክፈል ግዴታ መሆኑን አስገንዝበዋል።