ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቀጨኔ–አምባሳደር–ጊዮን-ኢሬቻ–ባምቢስ የወንዝ ዳርቻ ልማትን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ የ351 ሄክታር አጠቃላይ ስፋት እና የ10 ኪ.ሜ ርዝማኔ ያለው የኮሪደር ልማት ዘመናዊ፣ አረንጓዴ እና ሁሉንም አካታች የሆነች አዲስ አበባን የመገንባት ራዕያችንን እውን የሚያደርግ ትልቅ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
በዘመናዊ መሠረተ ልማት የታጀበው ይህ ፕሮጀክት በቂ የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች እና ከ100 በላይ መኪኖችን በአንድ ጊዜ መሙላት የሚያስችሉ ስምንት የኤሌክትሪክ መኪና መሙያ ማዕከላት እንዳሉትም ገልጸዋል።
በተጨማሪም በወንዝ አስተዳደር፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃ እንዲሁም በወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ ስፍራዎች አማካኝነት የአካባቢ ጥበቃን ከከተማ ገፅታ ለውጥ ጋር ማቀናጀት ተችሏል ብለዋል፡፡
ልማቱ አካባቢያዊ ገፅታውን ከማሳደግ ባለፈ አዳዲስ የኢኮኖሚ ዕድሎችን የፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል።
የተዘጋጀው የገበያ ማዕከል ቀደም ሲል በወንዝ ዳርቻው ይኖሩ ለነበሩ ነዋሪዎች የዕደ ጥበብ ምርቶችን እንዲያመርቱ፣ ለማሳያና ለመሸጫ እንዲጠቀሙበት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ በውስጡ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶችን፤ እንዲሁም የተቀናጁ የስፖርት መሰረተ ልማቶችን የያዘ በመሆኑ ለኑሮ ተስማሚና ተደራሽ የሆነ የከተማ ከባቢን እንደሚፈጥር አመልክተዋል፡፡
የልጆች መጫወቻ ስፍራዎች፣ ፕላዛዎችና አምፊ ቲያትሮች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች እንዲሁም የውሀ ትሪዒት ማሳያዎች ለመዝናኛና ማህበራዊ ግንኙነት አዲስ ዕድል እንደሚፈጥሩም ገልጸዋል፡፡
