InternationalNews

በስፔን ቢያንስ ስልሳ ስምንት ሰዎችን ለቀጠፈው አሰቃቂ የባቡር አደጋ ይፋዊ የሦስት ቀናት ብሔራዊ ሐዘን የታወጀ ሲሆን፥ በዋና ከተማዋ ማድሪድ ደግሞ በክስተቱ የተቆጡ ሰልፈኞች ከፖሊስ ጋር  ግጭት ውስጥ መግባታቸው ተሰምቷል።

የሀገሪቱ የትራንስፖርት ሚኒስትር እንደገለጹት፥ አደጋው የደረሰው ማድሪድ የሚገኘው የቁጥጥር ማዕከል በኮምፒውተር መስተጓጎል ምክንያት በቆመው ባቡር ላይ ሌላኛው ባቡር ያለምንም የፍጥነት ገደብ እንዲጓዝ የተሳሳተ ትዕዛዝ በማስተላለፉ ነው።

በዚህ የደህንነት ክፍተት የተቆጡ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በትራንስፖርት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አጠገብ ባደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ፥ የጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝን እና የባለሥልጣናቱን በአስቸኳይ ስልጣን መልቀቅ  ጠይቀዋል።

ይህ አሰቃቂ ክስተት በአሥር ወራት ውስጥ በሀገሪቱ የተመዘገበ ሁለተኛው ትልቅ አደጋ ሲሆን፥አደጋው በተመሳሳይ ኩባንያ በሚተዳደሩ ፈጣን ባቡሮችና በተመሳሳይ መስመር ላይ መከሰቱ ጥያቄ ፈጥሯል ነው የተባለው።

የአደጋውን መከሰት ተከትሎ አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ ያዘጋጁትን የቅስቀሳ መርሃ-ግብር የሰረዙ ሲሆን፥ የባቡር አሽከርካሪዎች ማኅበር በበኩሉ የባቡር መሠረተ ልማት ደህንነት እንዲጠበቅ በመጠየቅ የሥራ ማቆም አድማ ጀምሯል።

የአውሮፓ ሕብረት ለስፔን ሕዝብ ያለውን አብሮነት ለማሳየት በብራስልስ የሚገኙ ሰንደቅ ዓላማዎችን ዝቅ አድርጎ እንዲያውለበልብ ያዘዘ ሲሆን፥ የሀገሪቱ የሲቪል ጥበቃ ኃይል በበኩሉ የጠፉ ሰዎችን የማንነት ማረጋገጫ የዲ ኤን ኤ ናሙናዎችን መሰብሰብ ጀምሯል።