የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በትግራይ ክልል ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት ከ 68 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመድሃኒት፣ የምግብና የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
ከዚህ ውስጥ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመተው አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ሲሆን ይህም 240 ኩንታል የስንዴ ዱቄት፣ 720 ሊትር የምግብ ዘይት እና 7 ኩንታል ጨውን ያካተተና ለ1 ሺህ 600 በአዋሽ ሆስፒታል ለሚገኙ ጉዳተኞች ለአንድ ወር የሚያገለግል ድጋፍ መሆኑም ተገልጿል።
በተጨማሪም ማኅበሩ ከእንግሊዝ መንግስት የውጭ የጋራ ብልጽግና እና የልማት ቢሮ ያገኛቸው ከ56 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ መድሃኒቶችን ለስድስት ጤና ጣቢያዎች መከፋፈላቸውና ድጋፉ ለቀጣይ ሁለት ዓመታት እንደሚቀጥል ተጠቁሟል፡፡
በርክክቡ ወቅት የማኅበሩ ፕሬዘዳንት አበራ ቶላ የቀረበው ድጋፍ ካለው ሰፊ ፍላጎት አንጻር ውስን ቢሆንም፣ ማኅበሩ ከተጎዱ ማኅበረሰቦች፣ ከአካባቢው ህብረተሰብና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን ሰብዓዊ ድጋፉን ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
በማኅበሩ የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤትን የሰብዓዊ ምላሽ አቅሙን ለማጠናከርና ከማኅበረሰቡና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ለተጎጂዎች የሚደረገውን ድጋፍ ለማሳደግ ማኅበሩ ቁርጠኛ መሆኑም ተገልጿል።
