EthiopiaNews

በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የዋጋ ግሽበቱ በሁለት አሃዝ ሊቀጥል እንደሚችል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ አሳውቋል፡፡

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ስምንተኛ ስብሰባውን በማካሄድ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ በዛሬው ዕለት ባሳወቀበት መግለጫው ነው ይህ የተጠቆመው፡፡

በመስከረም ወር 2019 ለታየው የ14 ነጥብ 9 በመቶ የዋጋ ግሽበት በተለይ የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ከአቅርቦት ጋር በተያያዘ ያሳደረው ተጽዕኖ አስተዋጽኦ ማድረጉንም ባንኩ ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል፡፡

የምግብ ዋጋ ግሽበት በሰኔ ወር 2018 ከተመዘገበው 15 ነጥብ 1 በመቶ ወደ 14 ነጥብ 8 በመቶ የቀነሰ ቢሆንም ምግብ ነክ ያልሆነ የዋጋ ግሽበት ደግሞ ከ12 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 15 ነጥብ 1 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልጿል፡፡

በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በመካከለኛ ጊዜ ለማሳካት የያዝውን የነጠላ አሃዝ የዋጋ ግሽበት እቅድ ለማሳካት ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ አቅጣጫ ያስቀመተው፡፡