EthiopiaNews

የጤና ሚኒስቴር ከ30 ሺ በላይ ተሳታፊዎች የሚታደሙበት 5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የማህብረሰብ ጤና ጉባኤ ከኅዳር 14 እስከ 18 2019 አ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ አስታወቀ።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ይሄን ያሉት ከአፍሪካ ሲዲሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጂያን ካሲያ ጋር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።

የጤና ሚኒስትሯ በአዲስ አባባ ለሚካሄደዉ 5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የማህብረሰብ ጤና ጉባኤ በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ከኅዳር 14 እስከ 18 በአዲስ አበባ የሚካሄደው ጉባኤ በጤና ሚኒስቴር እና በአፍሪካ ሲዲሲ ትብብር መዘጋጀቱን ገልፀው ጉባኤው ቀጠናዊ የጤና ትብብርን የሚያጠናክር እና የጋራ የጤና ችግሮቻችንን በጋራ የምንፈታበት ነው ብለዋል፡፡

ጉባኤው የጤና ስርአታችንን ለሌሎች የምናሳይበት እና ከሌሎች ሃገራትም የልምድ ልውውጥ የምናደርግበት ነው ያሉት ዶ/ር መቅደስ፤ የሃገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ፣ የጤና ዲጂታይዜሽን እና የጤና ቱሪዝምን ለማስፋፋት የአፍሪካ ሃገራት የሚመክሩበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የአፍሪካ ሲዲሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጂያን ካሲያ በጉባኤው የጤና አውደርእይ እንደሚቀርብ ገልፀው ጉባዔው የአፍሪካ የጤና ዘርፍ የደረሰበትን ደረጃ የምናሳይበት መድረክ ነው ብለዋል፡፡

በጉባኤው ከ30 ሺ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን ከ1 ሺህ በላይ ጥናታዊ ጽሁፎች እንደሚቀርቡ ይጠበቃል፡፡