የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የውሃ አምራቾች ማህበር የታሸጉ ውሃዎች የቸርቻሪዎች መሸጫ ዋጋ ይፋ ማድረጋቸውን አስታወቀ።
ቢሮው ይሄን ያለው ዛሬ ባወጣው መግለጫ ነው።
በመዲናዋ ያሉ የታሸጉ የውሃ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ በተመለከተ የታሸገ ውሃ አምራቾች በማህበራቸው በኩል ለንግድ ቢሮ ማሳወቃቸውን ገልጿል።
በዚህም 1 ሊትር የታሸገ ውሃ ከ35 ብር – 41ብር ከ66 ሳንቲም ፣ 2 ሊትር ውሃ ከ40 ብር -50 ብር 33 ሳንቲም ፣ ግማሽ ሊትር ውሃ ከ6 ብር – 25 ብር ከ17 ሳንቲም እና ሩብ ሊትር ውሃ ከ17 ብር 53 ሳንቲም – 20 ብር ከ84 ሳንቲም ተተምኗል።
ቢሮው በሸማቾች ጥበቃ አዋጅ 813/2006 ማንኛውም ነጋዴ የሚሸጣቸውን ምርቶች ዋጋ በሚታይ ቦታ የመለጠፍ/ለሸማቾች የማሳወቅ ግዴታ የሚጥልበት መሆኑን አስታውሶ ዋጋቸውን ያላሳወቁ የውሃ አምራች ፋብሪካዎች በሁለት ቀናት ውስጥ ዋጋ እንዲያሳውቁ ተብሏል።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ሀቢባ ሲራጅ በአዋጁ መሠረት የመሸጫ ዋጋቸውን ያላሳወቁ የውሃ አምራች ድርጅቶች ውሃዎችን በመዲናዋ መቸርቸር እንደማይችሉ ገልፀው በተሰጠው የጊዜ ገደብ እንዲያሳውቁ አሳስበዋል።
ኃላፊዋ በመዲናዋ ውሃ በቦቴ እያዞሩ የሚሸጡ ድርጅቶችን በተመለከተ በቅርቡ ከአዲስ አበባ ውሃ አገልግሎት ድርጅት ጋር በመነጋገር መፍትህ እንደሚሰጥበት አሳውቀዋል።
በመጨረሻም የታሸጉ ውሃዎች ዝርዝር ዋጋ ከዚህ ልጥፍ ጋር የተያያዘ ሲሆን የንግድ ቢሮ የቁጥጥር ሠራተኞች ፋብሪካዎቹ ባሳወቁት ዋጋ መሠረት ሽያጭ እየተፈፀመ መሆኑን የመከታተል ስራ እንዲያከናውኑ ኃላፊዋ አሳስበዋል።
