EthiopiaNews

በምሥራቅ አፍሪካ በኤልኒኖ ሳቢያ እንስሳት እና ሰውን የሚያጠቃ ወረርሽኝ ሊከሰት ይችላል ሲሉ ፋኦ እና ኢጋድ አስጠነቀቁ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ፋኦ እንዲሁም የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ኢጋድ በኤልኒኖ ምክንያት የሚከሰተው ከፍተኛ ዝናብና ጎርፍ በምሥራቅ አፍሪካ ሪፍት ቫሊ ፌቨር በመባል የሚታወቀው እንስሳት እና ሰውን የሚያጠቃ ወረርሽኝ የመከሰት አደጋ እየጨመረ መሆኑን አስጠንቅቀዋል፡፡

ለበሽታው ተጋላጭ ከሆኑ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያና ኡጋንዳ እንደሚገኙበት የተገለጸ ሲሆን በሽታው በቫይረስ የሚመጣ እና በዋነኝነት እንስሳትን የሚያጠቃ ቢሆንም ወደ ሰዎችም ሊተላለፍ የሚችል ነው ተብሏል፡፡

በተያዘው ዓመት ከጥቅምት እስከ ጥር ድረስ በአብዛኛው የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ከመደበኛው በላይ ዝናብ እንደሚጠበቅ ትንበያዎች የሚያመለክቱ ሲሆን ይህም የትንኞችን መራቢያ አካባቢ በማስፋት የበሽታውን ስርጭት ሊያሳድግ ይችላል ነው የተባለው፡፡

በዚህም ሀገራት የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል ክትትል እንዲያደርጉና ክትባቶችን አስቀድመው እንዲያዘጋጁም ጥሪ አቅርበዋል፡፡