የአዲስ አበባ ፖሊስ በተለምዶ ‘ትፍታ ‘ የተባለውን የማታለል ወንጀል የፈፀመ አንድ ተጠርጣሪ ግለሰብን በቁጥጥር ስር አዋለ።
አንተነህ ጌታቸዉ የተባለዉ ተጠርጣሪ የወንጀል ድርጊቱን የፈፀመዉ ጥቅምት 22 ቀን 2019 ዓ/ም ከቀኑ 8:00 ሠዓት በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 03 ልዩ ቦታው ሻላ መናፈሻ የተባለ አካባቢ እንደሆነ ፖሊስ ገልጿል፡፡
የቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ የወንጀል ምርመራ ም/ዋና መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ኤፍሬም ዓለሙ ተጠርጣሪ አንተነህ ጌታቸው የግል ተበዳይ አቶ ፋብያን ንጉዲ የተባሉ ጀርመናዊው ግለሰብ ላይ ምራቅ ከተፋ በኋላ ይቅርታ በማለት ልብሱን በመጥረግ ከኪሱ ውስጥ ግምቱ 140ሺህ ብር የሚያወጣ አይፎን 13 pro max ስልክ ይዞ ተሰውሯል፡፡
የግል ተበዳይም የተፈፀመባቸውን ድርጊት በቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ ለአደይ አበባ አካባቢ ፖሊስ መምሪያ በማመልከታቸው ተገቢው ክትትል ሲደረግ ነበር ያሉት ኮማንደር ኤፍሬም ተጠርጣሪው ከሚጠቀምበት የሠሌዳ ቁጥር B61211 አ/አ ቶዮታ ኤክስኪዩቲቭ ተሽከርካሪ ጋር በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ኃላፊው ገልፀዋል፡፡
በተጠርጣሪው ላይ ተጨማሪ ምርመራ የማስፋት ተግባር እንደሚቀጥል ያስታወቁት ኮማንደር ኤፍሬም በግለሰቡና በተሽከርካሪው ወንጀል የተፈፀመበት ማንኛውም ግለሰብ ቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ በመምጣት ጥቆማ መስጠት የሚችል መሆኑንም ገልፀዋል።
