የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር የተጠረጠሩ ሦስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታወቀ።
መልካሙ አስማረ፣ ዋናው አደመና አብዱረህማን ሀሰን የተባሉ ተጠርጣሪዎች ህገ ወጥ የጦር መሣሪያ ሲያዘዋውሩ በቁጥጥር ስር የዋሉት በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው ዋይ ዜድ የገበያ ማዕከል አካባቢ መሆኑን ፖሊስ ገልጿል።
ተጠርጣሪዎቹ የሠሌዳ ቁጥር ኮድ 1-24770 አ/አ የሆነ ላዳ ተሽከርካሪ በመጠቀም 1 ሺህ 4መቶ 54 የክላሽና 1መቶ የብሬን ጥይት እየጫኑ ሳለ በስፍራው መደበኛ ስራቸውን ሲያከናውኑ በነበሩ የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታውቋል።
ህገ ወጥ የጦር መሣሪያውን እና ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ያዋሉትን የፖሊስ አባላትን በ5መቶ ሺህ ብር ለመደለል ጥይቶቹን እንዲለቁላቸው የተጠየቁት የፖሊስ አባላት ተቋምና ህዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነት በገንዘብ እንደማይቀይሩ በመግለፅ ተጠርጣሪዎቹን ወደ ዋና መምሪያው ይዘው መምጣታቸው ተገልጿል።
የህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በሀገር ሠላምና ፀጥታ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑን በመረዳት ሁሉም ዜጋ ድርጊቱን መከላከልና ማውገዝ እንደሚገባው ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል።
