አዋሽ ኢንሹራንስ አ.ማ አክሲዮኖቹን በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በይፋ ማስመዝገብ መቻሉን አስታወቀ።
አዋሽ ኢንሹራንስ በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ላይ በመመዝገብ የመጀመሪያው መድን ድርጅት በመሆን ነው የምዝገባ ማረጋገጫ የዕውቅና ሰርተፍኬት የተቀበለው።
በገበያው ላይ “AWIN” በሚል መለያ ምልክት የቀረበው አዋሽ ኢንሹራንስ ከ6 ሚሊዮን 750 ሺህ በላይ የተመዘገቡ አክሲዮኖችን ይዞ ነው ወደ ዋናው ገበያ መቀላቀሉ የተጠቀሰው።
በዛሬው ዕለት በይፋ ምዝገባውን ያከናወነው አዋሽ ኢንሹራንስን ጨምሮ ስምንት የፋይናንስ ተቋማት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ነባርና አዳዲስ አክሲዮኖቻቸውን በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያው ማስመዝገባቸውም ይገለጻል፡፡
ይህ ምዝገባ ለኢንሹራንስ ኩባንያው ተጨማሪ ካፒታል የማሰባሰብ ዕድል የሚፈጥር መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮዲት ካሳ አዋሽ ኢንሹራንስ ገበያውን መቀላቀሉ ቀደም ሲል በባንክና በቴሌኮም ዘርፎች ላይ ብቻ ተወስኖ የነበረውን የካፒታል ፍሰት ወደ መድን ዘርፍ ለማስፋት የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል።
