ሩሲያ እና ዩክሬን የአሜሪካ ተደራዳሪዎች ሞስኮ ከመድረሳቸው በፊት በየመዲናዎቻቸው ላይ የአየር እና የድሮን ጥቃት መለዋወጣቸው ተሰምቷል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና ጃሬድ ኩሽነር ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ለመምከር ዛሬ ማለዳ ሞስኮ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሰዋል።
ይህ የሆነው በአቡ ዳቢ የተካሄደው የሁለት ቀናት የሰላም ውይይት በእስረኞች ልውውጥ ስምምነት ቢጠናቀቅም፣ በግዛትና ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ልዩነቶች አሁንም እንዳሉ ከተገለጸ በኋላ ነው።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በዩክሬን መዲና ኪየቭ የሚገኝ የጦር መሣሪያ መጋዘን እና የኃይል ማመንጫ ተቋማትን መምታቱን ሲያስታውቅ፣ የሞስኮ ከንቲባ በበኩላቸው ወደ ሩሲያ መዲና ሲያመሩ የነበሩ አምስት የዩክሬን ድሮኖችን በአየር መከላከያ መምታታቸውን ገልጸዋል።
