የአዲስ አበባ ፖሊስ ከ5መቶ ሺ ብር በላይ የሚያወጡ ንብረቶችን ከጋራዥ በመስረቅ እና በመቀበል የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታወቀ።
ሃያቱ ግላኝ እና ገመዳ ከበደ የተባሉት ሁለት ተጠርጣሪዎች ጥቅምት 29 ቀን 2019 ዓ.ም ከምሽቱ 4 ሰዓት በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 6 ሃብትሽ ጋራዥ ከሚባል ስፍራ የወንጀል ድርጊቱን መፈጸማቸውን ነው ፖሊስ ያስታወቀው።
ሃያቱ ግላኝ የተባለው ተጠርጣሪ በጥበቃ ስራ ተቀጥሮ ከሚሰራበት ጋራዥ የተጣለበትን እምነት ወደጎን በማለት ጀነሬተር፣ ፍሪጅ እና ሌሎች ንብረቶችን በመስረቅ መሰወሩን ፖሊስ አስታውቋል።
ፖሊስ ከግል ተበዳይ የደረሰውን የክስ አቤቱታ መነሻ በማድረግ የምርመራ እና የክትትል ስራውን በመጀመር ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር አውሎ ባከናወነው ምርመራ የማስፋት ተግባር ገመዳ ከበደ ወደተባለው ተቀባይ በመሄድ ከነኤግዚቢቱ በቁጥጥር ስር ማዋል ችሏል።
ሁለቱን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር በማዋል በማስረጃ የተደገፈ ምርመራ በማድረግ በህግ አግብብ እንዲቀጡ እየሰራ እንደሚገኝ ፖሊስ ገልጿል።
ጥበቃ ቀጥረው የሚያሰሩ ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦች ከቅጥር ጀምሮ ህጋዊ ሂደትን መከተል እና ከቀጠሩም በኋላ በቂ ክትትል እና ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል።
መረጃው ከአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የተገኘ ነው።
