የመድኃኒት አምራቹ ቤዬር ኤጂ የሚያመርታቸውን መድሃኒቶች ከማቅረብ ባሻገር ምግብ እና ስነምግብን የሚደግፉ ምርቶችን በኢትዮጵያ ለማምረት ማቀዱን አስታወቀ።
የቤዬር ኤጂ ዋና ስራ አስፈፃሚ ቢል አንደርሰን ይሄን ያሉት ከጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ነው።
ዋና ስራ አስፈፃሚው ኩባንያቸው በኢትዮጵያ እያደረገ የሚገኘውን የስነ-ምግብ እና የእናቶች ጤና ማሻሻል ስራዎችን ይበልጥ በማጠናከር እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ኩባንያው የሚያመርታቸውን መድሃኒቶች ከማቅረብ ባሻገር ምግብ እና ስነምግብን የሚደግፉ ምርቶችን በኢትዮጵያ ለማምረት ማቀዱን ያስረዱት የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ለጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ስነ-ምግብ እና ተዋልዶ ጤና ስልጠና ለመስጠት ማቀዱንም ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስቴር እና ቤዬር ኤጂ በምግብ እና ስነ-ምግብ፣ የእናቶችን ሞት መቀነስ እና የመድኃኒት አቅርቦትን ማሻሻል ላይ በቅርበት ሲሰሩ መቆየታቸውን ያስታወቁት የጤና ሚኒስትሯ ተለዋዋጭ የሆነውን አለም አቀፍ የመድኃኒት አቅርቦት መቋቋም እና የሀገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ አስፈላጊነትን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በተጨማሪም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ጫና ለመቀነስ ከቤዬር ኤጂ ጋር ያለውን ትብብር ማጠናከር እንደሚፈልጉ ዶ/ር መቅደስ ለልዑካኑ ያስረዱ ሲሆን፤ የመድኃኒት አምራቾች ምርት በኢትዮጵያ እንዲጀምሩ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን በመዘርዘር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
