EthiopiaNews

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ አፈጻጸም ከ78 በመቶ በላይ መድረሱን አስታወቀ።

ተቋሙ ይሄን ያለው የመጀመሪያውን ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸም በገመገመበት ጊዜ ነው።

የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አፈጻጸም 78 ነጥብ 36 በመቶ መድረሱ ተገልጿል።

በሩብ ዓመቱ ለመሙላት ከታቀደው 255 ሺህ ሜትር ኪዩብ የአርሲሲ ኮንክሪት ሙሌት 250 ሺህ ሜትር ኪዩብ የተከናወነ ሲሆን ከአጠቃላዩ 6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የአርሲሲ ኮንክሪት ሙሌት ውስጥ 82 ነጥብ 29 በመቶው ተሞልቷል፡፡

ግድቡ ሲጠናቀቅ ከሚኖረው የ201 ነጥብ 5 ሜትር ቁመት ውስጥ በአሁኑ ወቅት የግድቡ የግራ ክንፍ 145 ሜትር እንዲሁም የቀሪ ክፍሎቹ አማካይ ቁመት 138ሜ ማድረስ ተችሏል::

የኃይል ማመንጫ ቤቱ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 1 ነጥብ 87 ሺህ ሜትር ኪዩብ እንዲሁም የውኃ ማስተንፈሻ(ስፒልዌይ) በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 17 ነጥብ 34 ሺህ ሜትር ኪዩብ የስትራክቸራል ኮንክሪት ሙሌት ተከናውኗል::

የስድስት ተርባይኖች የኤሌክትሮሜካኒካል ሥራዎች ዕቃዎች ግዥ፣ የማጓጓዝ፣ የመገጣጠም እና የተከላ ሥራዎች በመርሃ-ግብሩ መሠረት እየተከናወነ መሆኑም ተገልጿል።

የግድብ ውኃ ማስተንፈሻና ማስተላለፊያ ቱቦዎችግዥ፣ የማምረት፣ እቃዎችን የማጓጓዝ፣ የመገጣጠም እና የተከላ ሥራዎች በታቀደው መሠረት እየተከናወነ ይገኛል፡፡