EthiopiaNews

በአዲስ አበባ ከነገ ሕዳር 11 እስከ ሕዳር 14 ቀን 2019ዓ.ም ድረስ ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ሕጻናት የፖሊዮ መከላከያ ክትባት እንደሚሰጥ የከተማዋ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የልጅነት ልምሻ ወይም ፖሊዮ ቫይረስ በተበከለ ምግብና ውሃ አማካኝት የሚመጣ እና ሕፃናትን ለዘላቂ የእጅ፣ እግርና የአካል መልፈስፈስ የሚዳርግ ነው ያለው ቢሮ፤ በሽታውን መከላከል የሚቻለው በመደበኛ እና በዘመቻ መልክ በሚሰጥ ክትባት ብቻ መሆኑን ገልጿል።

ሕጻናት በተገቢው ጊዜ ክትባት ካላገኙ በበሽታው ሳቢያ ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉም አሳስቧል።

ቢሮው ክትባቱን ከነገ ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት ቤት ለቤት፣ በመጠለያ ጣቢያዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በቅድመ መደበኛ እና በህፃናት ማቆያዎች እንዲሁም ህፃናት በሚገኙበት ቦታዎች ሁሉ እንደሚሰጥ አስታውቋል።

እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሁሉም ሕፃናት ከዚህ በፊት ቢከተቡም ባይከተቡም በዘመቻው የሚሰጠውን ክትባት እንዲከተቡ ያሳሰበው ቢሮው፤ ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች  ህጻናትን በማስከተብ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡም አደራ ብሏል።