ትኩረት ለዲስሌክሲያ ሰለባዎች
ዲስሌክሲያ በተሰኘው የአካል ጉዳት ሰለባ ለሆኑ ታዳጊዎች የሚደረገው ድጋፍ አነስተኛ ነው ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ገልጿል።
ዲስሌክሲያ የተሰኘው የአካል ጉዳት በቋንቋ ላይ የተመሠረተ የመማርና የማንበብ ችሎታዎች እድገት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድርና ከነርቭ መዛባት የሚመነጭ እክል ሲሆን ተቀራራቢ ቅርጽ ያላቸውን ፊደላት የመለየት ችግር መሆኑንም ኮሚሽኑ አመልክቷል።
ይሁንና ዲስሌክሲያን አስመልክቶ በመምህራን፣ ተማሪዎችና ወላጆች ዘንድ ግንዛቤ ባለመኖሩ ወይም በጣም አናሳ በመሆኑ ችግሩ ያለባቸው ተማሪዎች እንደ ሰነፍና ረባሽ ተማሪ ከመቆጠራቸው ባሻገር አስፈላጊውን እገዛ ባለማግኘታቸውና ቁጣና ነቀፋ ስለሚደርስባቸው በዕድሜ ከፍ እያሉ ሲሄዱ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ይገደዳሉ ተብሏል።
በመሆኑም እ.ኤ.አ. በ2025 የሚጠናቀቀው የኢትዮጵያ የልዩ ፍላጎት ትምህርት መሪ ዕቅድ በኢትዮጵያ ድህነት፣ ጾታ፣ ዘር፣ ቋንቋ፣ የመማር እክል ሳይገድበው ለሁሉም ተማሪዎች ክፍት የሆነ የትምህርት ሥርዓት ተደራሽ ማድረግን ያለመ በመሆኑ በዚህ ረገድ ፍትሀዊ የትምህርት ሥርዓት መዘርጋትን መንግሥት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ገልጿል።