የኢትዮጵያ የፋይናንስ ሪፎርም
የኢትዮጵያ የፋይናንስ ሪፎርም እርምጃዎች በውጭ አካላት የተጫኑ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ሀገራዊ ባለቤትነት ያላቸው፣ በፍላጎት ላይ የተመሰረቱ እና ከሀገሪቱ የልማት ቅድሚያ ግቦች ጋር የተዛመዱ መሆናቸው ተገልጿል።
ይህ የተገለጸው በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ ባለው የ2026ቱ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና የዓለም ባንክ የፀደይ ስብሰባ ጎን ለጎን በተዘጋጀ መድረክ ላይ ሲሆን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ ለዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም እና ለአውሮፓ ሕብረት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በዘርፉ ላይ ሰፋ ያለ ማብራርያ ሰጥተዋል ።
የብሔራዊ ባንኩ ገዢ በመድረኩ፤ ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ማዕቀፍ ውስጥ እያካሄደች ያለውን የፋይናንስ ዘርፍ የሪፎርም አጀንዳ እና መዋቅራዊ ሽግግርን በማብራርያቸው አቅርበዋል።
ዶ/ር ኢዮብ በንግግራቸው፣ ኢትዮጵያ ወለድ ምጣኔ ላይ የተመሰረተ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ እና ወደ ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት ያደረገችውን ሽግግር አብራርተዋል።
በቀጣይም የሀገር ውስጥ የፋይናንስ ገበያን ይበልጥ ማሳደግ እና ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ማድረግ ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
አክለውም ዘላቂነት ያለው እድገት ለማምጣት ጠንካራ የተቋም አቅም መገንባት፣ የፖሊሲ ቀጣይነትን ማረጋገጥ እና እያደገ የመጣውን የግሉን ዘርፍ የሚደግፍ የፋይናንስ ሥርዓት መፍጠር ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።
#EBS
#EBSTVNEWS
#EBSTVSPORT
#_7696_WN
https://t.me/ebstvnews
https://ebstv.tv/
