በጎዴ እየተገነባ ያለው የማዳበሪያ ፋብሪካ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጎዴ እየተገነባ የሚገኘው በዓመት 3 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ዩሪያ ማዳበሪያ የማምረት ዐቅም ያለው ፋብሪካ ግንባታ በተያዘለት ዕቅድ መሠረት እየተከናወነ መሆኑን አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአሊኮ ዳንጎቴ ጋር በመሆን በጎዴ ሥራው የደረሰበትን ደረጃ የገመገሙ ሲሆን በፕሮጀክቱ ስፍራ የሚታየው የሥራ ሂደቱ ፍጥነት አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ የምግብ ሉዓላዊነት፣ የኢንዱስትሪ እድገት እና በኢኮኖሚ ራስን የመቻል ጥረት ውስጥ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለው ኢንቨስትመንት መሆኑንም አስረድተዋል።
የማዳበሪያ ፋብሪካው በሚጠናቀቅበት ወቅት የሀገር ውስጥ የማምረት ዐቅምን ያጎለብታል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ከውጭ በሚገባ ማዳበሪያ ላይ ያለውን ጥገኝነት በመቀነስ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አርሶአደሮችን ይደግፋል ብለዋል።
እንዲሁም ለኢንቨስትመንት እና የሥራ ዕድል ፈጠራም አዳዲስ እድሎችን ይከፍታል ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልፀዋል።
