የምሽት ፀብ ህይወት ቀጠፈ
የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በአንድ የምሽት መዝናኛ ቤት ውስጥ በተፈጠረ ፀብ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን አስታወቀ፡፡
ግንቦት 30 ቀን 2018 ዓ/ም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ቱሉ ዲምቱ አካባቢ በሚገኝ ሆልስቴ ሆቴል ውስጥ ሲዝናኑ በነበሩ ሰዎች መካከል በተፈጠረ ፀብ አቡሽ ባዩ የተባለ ግለሰብ በሽጉጥ ተመትቶ ሕይወቱ ማለፉን ፖሊስ ገልጿል፡፡
ፖሊስ ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ 12 ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራውን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በፀቡ ተሳትፎ የነበረውን አንድ ግለሰብ፣ ከገዳዮች ጋር አብሮ ሲዝናና የነበረን ሌላ ተጠርጣሪ እንዲሁም ለፀቡ መንስኤ እንደሆነች የተጠረጠረች አንዲት አስተናጋጅ ከተያዙት መካከል እንደሚገኙበት ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በግለሰቦች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት በሰዎችና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን እና ገዳይ ሟች ታጥቆት የነበረን ሽጉጥ ቀምቶ እንደገደለው አመላካች ማስረጃዎችን ማግኘቱን ፖሊስ ገልፆ ወደ ፊት የምርመራ ውጤቱን ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
ከዚህ የወንጀል ድርጊት ጋር በተያያዘ በማህበራዊ ሚዲያ የተዛባና የከተማችንን አሁናዊ የፀጥታ ሁኔታ የማይገልፅ መረጃ እየተሰራጨ እንደሆነ እና ማህበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም ስጋት ለመፍጠር የሚደረጉ አላስፈላጊ ድርጊቶችን ለመግታት ህብረተሰቡ እውነተኛውን መረጃ ከትክክለኛው የመረጃ ምንጭ የመቀበል ልምድን ሊያዳበር እንደሚገባ ፖሊስ መልእክት አስተላልፏል።
#EBS
#EBSTVNEWS
#EBSTVSPORT
#_7696_WN
https://t.me/ebstvnews
