Sports

EBS SPORT – አጫጭር የኢቢኤስ ስፖርት ዘገባዎች – ግንቦት 12 / 2014

👉🏾 በዓለም ዋንጫ አፍሪካን ወክለው የሚሳተፉ ዳኞች ይፋ ሲደረጉ የኢትዮጵያዊው ዳኛ ባምላክ ስማቸው ሳይካተት ቀርቷል። በመጪው ዓመት በኳታር አዘጋጅነት ለሚካሄደው ውድድር 36 ዋና ዳኞችን፣ 69 ረዳት ዳኞችን እና 24 የቫር ዳኞች ውድድሩን እንዲመሩ መመረጣቸው ይፋ ሆኗል። ከነዛ መሀከል ግን ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ ስማቸው በዝርዝሩ ሳይካተት መቅረቱ ታውቋል። በሌላ በኩል በውድድሩ አፍሪካን ወክለው ጨዋታዎችን እንዲመሩ ስድስት ዋና ዳኞች መመረጣቸው ይፋ ሆኗል። 1

👉🏾 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር 24ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን የስነምግባር ሂደቶች በተመለከተ ውሳኔዎችን ተላልፈዋል፡፡ ውሳኔው የተላለፈውም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ በትናንትናው ዕለት ሐሙስ ባደረገው ስብሰባ ነው፡፡ በስብሰባውም ኮሚቴው በ24ኛ ሳምንት የተደረጉ ጨዋታዎችን ጨምሮ ሌሎች ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ሪፖርቶች መርምሯል፡፡ ከዛም ጥፋት ፈፅመዋል ባላቸው የሚጉ ተጫዋቾች ላይ የቅጣት ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ በስብሰባው ላይ ከዳኝነት አንፃር የቀረበውን ክስ መሰረት በማድረግም ውሳኔ እንዲሰጥበት ለብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ተላልፎ ነበር። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴም ሶስት የውድድሩን ዳኞች ለጊዜው ውድድሩ ከሚካሄድበት ባህር ዳር ከተማ ወደ መጡበት ከተማ እንዲመለሱ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ቀጣይ ውሳኔዎችንም በተመለከተም በሂደት እንደሚገልፅ ለፕሪሚየር ሊጉ የውድድርና ስነ ስርዓት ኮሚቴ በላከው ምላሽ አስታውቋል።  2

👉🏾 ፖል ፖግባ የማንችስተር ሲቲን የዝውውር ጥያቄ በመጨረሻ ውድቅ ማድረጉ ተሰምቷል፡፡ ፈረንሳዊው አማካኝ ለረጅም ጊዜያት ከክለቡ እንደሚለቅ ሲነገር የቆየ ሲሆን ስሙም ከተለያዩ የአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች ጋር ሲያያዝ ከርሟል፡፡ አሁን ላይ ፖግባ ከማንችስተር ሲቲ ጋር በግላዊ ጥቅማጥቅሞች ዙሪያ ከስምምነት ላይ ቢደርስም የክለቡን ደጋፊዎች ፍራቻ ወደኢትሀድ ሊያደርግ የነበረውን ዝውውሩን ውድቅ ማድረጉ ታውቋል፡፡ አማካኙ በዘንድሮው የውድድር ዘመን 20 የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን ሲያደርግ ያስቆጠረውም አንድ ግብ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ፖግባ ወደጎረቤት ክለብ ሲቲ የሚደርገው ዝውውር ከደጋፊዎች በኩል ሊያመጣበት የሚችለውን እሳጣገባ ፍራቻ በመጨረሻ ጥያቄውን እንዳይበል እንዳደረገው ተሰምቷል፡፡  3

👉🏾 አንቶኒ ሩዲገር በቼልሲ በኩል የታየው መንቀራፈፍ ክለቡን ለመልቀቅ እንዳስገደደው ተናግሯል፡፡ ጀርመናዊው የመሀል ተከላካይ ይህን የተናገረው ወደሪያል ማድሪድ ማምራቱን በማስመልከት ባደረገው የስንብት ንግግር ላይ ነው፡፡ ሩዲገር በንግግሩ ክለቡ ከነሀሴ እስካለፈ ጥር ድረስ የውል ስምምነት ማራዘሚያ ሳያቀርብለት መቆየቱ ነገሮችን እንዳወሳሰባቸው ገልጿል፡፡ ተጫዋቹ በንግግሩ ከከልቡ በኩል የታየው ዝምታ የሌሎች ክለቦችን ጥያቄ እንዲሰማ ምክንያት እንደሆነውም ተናግሯል፡፡ ሩዲገር በዚሁ የስንብት ንግግሩ ለቼልሲ የተለየ ፍቅር እንዳለው ገልፆ የቼልሲና የለንደን ትዝታ አብሮት እንደሚዘልቅ ጨምሮ ገልጿል፡፡   4

👉🏾 የመርሲሳይዱ ክለብ ኤቨርተን ከሌጉ መውረድ የታደገውን ውጤት አስመዝግቧል፡፡ ትናንት ምሽት ከክሪስታል ፓላስ ጋር ጨዋታውን ያደረገው ክለቡ 3 ለ 2 በሆነ ውጤት ማሸነፉን ተከትሎ ወደታችኛው ሊግ የመውረድ ስጋቱን ቀርፏል፡፡ ውጤቱን ተከትሎም የእሁዱን ጨዋታ ሳይጠብቅ ከ 37 ጨዋታዎች 39 ነጥቦችን በመሰብሰብ 16ተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ከወራጅነት ቀጠናው መትረፍ ችሏል፡፡ በመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ከአርሰናል የሚጫወተው ክለቡ ድል ከቀናው ደረጃውን በአንድ ከፍ ማድረግ የሚችልበትን እድል ጭምር በእጁ አስገብቷል፡፡ በቀድሞው የቼልሲ ዝነኛ ተጫዋች እና አሰልጣኝ ፍረናክ ላምፓርድ እየተመራ የሚገኘው ኤቨርተን በዘንድሮው የውድድር ዘመን እጅግ ከባድ ጊዜን አሳልፏል፡፡  5

👉🏾 ስቴቨን ጄራርድ እሁድ ምሽት ከማንችስተር ሲቲ ጋር ለመፋለም ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ የሚታወቅበት የመጨረሻ ጨዋታ በመጪው እሁድ ሲደረግ ሲቲ የአንድ ነጥብ ብልጫ ይዞ በሜዳው አስቶን ቪላን ያስተናግዳል፡፡ እናም በተመሳሳይ ዎልቭስን በሜዳው የሚገጥመው ሊቨርፑል ተጋጣሚውን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን የሲቲንም ነጥብ መጣል ይፈልጋል፡፡ ከዛ ጋር ተያይዞ የእሁዱን ጨዋታ በማስመልከት አስተያየቱን የሰጠው የቀድሞው የሊቨርፑል አማካኝ እና የአሁኑ የቪላ አሰልጣኝ ጄራርድ ለእሁዱ ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡ ለቀድሞ ክለቡ ከ 700 በላይ ጨዋታን ያደረገው ጄራርድ በአስተያየቱ ልጆቹ ሲቲ ዋንጫውን እንዳያነሳ ሁኔታዎችን እንደሚያከብዱበት ያለውን እምነት ገልጿል፡፡ የሊጉ የመጨረሻ ሁሉም ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሰዓት እሁድ ምሽት 12 ሰዓት የሚካሄዱ ይሆናል፡፡    6

👉🏾 የሊቨርፑሉ ዲቮክ ኦሪጊ ወደኤሲ ሚላን ለማምራት ከስምምነት መድረሱ ተሰምቷል፡፡ በመጪው ክረምት በቀዮቹ ቤት ያለው የውል ስምምነት የሚጠናቀቀው ኦሪጊ ከረጅም ዓመታት ቆይታ በኋላ ክለቡን ለመሰናበት መቁረጡ ታውቋል፡፡ ያንን ተከትሎም ከ 2015 አንስቶ በሊቨርፑል የቆየውና ለክለቡ እጅግ የሚታወሱ ግቦችን ያስቆጠረው ሁለገብ ተጫዋች ዝውወሩን ለማጠናቀቅ የሕክምና ምርመራ እየተጠባበቀ እንደሚገኝ ተሰምቷል፡፡ ኦሪጊ በሊቨርፑል ቤት ቆይታው የቋሚ ተሰላፊነት እድል ያለማግኘቱን ሂደት ወደሚላን በማምራት ለመቀየር ማሰቡም ተያይዞ ተገልጿል፡፡ 7 ኤርሊንግ ሀላንድ ለክለብ አጋሮቹና ሰራተኞች የስንብት ስጦታ ማበርከቱ ተሰምቷል፡፡ ኖርዌያዊው የዶርትሙንድ ኮከብ በመጪው ክረምት ወደማንችስተር ሲቲ የሚመጣ መሆኑን ተከትሎ የክለቡን ደጋፊዎች ልብ በሚነካ ሁኔታ መሰናበቱ ይታወቃል፡፡ አሁን እንደተሰማው ደግሞ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ወጪ በማድረግ ለ 33 የክለቡ ተጫዋቾች እና 20 ሰራተኞች ውድ ሮሌክስ ሰዓት አበርክቷል፡፡ ሁለት አይነት ዝርያ ያላቸው ሰዓቶቹ እያንዳንዳቸው ከስድስት ሺህ እስከ ስምንት ሺህ እና ከ 11 ሺህ እስከ 13 ሺህ ፓውንድ ወጪ እንደተደረገባቸውም ታውቋል፡፡ ማንችስተር ሲቲ ተጫዋቹን ለማግኘት 51 ሚሊየን ፓውንድ ወጪ እንዳደረገ መግለጹ የሚታወቅ ሲሆን ተጫዋቹም በኢትሀድ ቤት ከፍተኛ ተከፋይ እንደሚሆን ተያይዞ ተነግሯል፡፡