የኢትዮ-አሜሪካ ትብብር
አሜሪካ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች፡፡
በዋሺንግተን ዲሲ ከተካሄደው የዓለም ባንክ እና የአይኤምኤፍ ስብሰባ ጎን ለጎን በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ከከፍተኛ የአሜሪካ የግምጃ ቤት መሥሪያ ቤት ባለሥልጣናት ጋር በኢኮኖሚያዊ ትብብር ዙሪያ መክሯል።
በዋነኝነት በአዲሱ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ስትራቴጂካዊ የኢንቨስትመንት ዕድሎች በስፋት የመከሩት ሀገራቱ ሌሎች የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነቶችን በማሳደግ ላይም ተወያይተዋል።
ሁለቱም ወገኖች ቅድሚያ በሚሰጧቸው የጋራ የኢኮኖሚ ጉዳዮችን ወደፊት ለማራመድ ዕድገትን ለማፋጠንና የሁለቱን አገራት የኢኮኖሚ ትስስር ለማስፋት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተነግሯል፡፡
የአሜሪካ ባለሥልጣናት አገራቸው ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን የምታደርገውን ድጋፍ በቴክኒክ ድጋፍ፣ በግሉ ዘርፍ ተሳትፎና ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመተባበር እንደምታጠናክር ማረጋገጣቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
#EBS
#EBSTVNEWS
#EBSTVSPORT
#_7696_WN
https://t.me/ebstvnews
www.ebstv.tv
