ሲያከራክር የሰነበተው የጉምሩክ ረቂቅ አዋጅ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ24ኛ መደበኛ ስብሰባው የጉምሩክ አዋጅን እንደገና ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጽድቋል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርት እና የውሳኔ ሀሳቡን ለምክር ቤቱ ያቀረበ ሲሆን አዋጁ የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር እንደሚያግዝም አብራርቷል፡፡
ረቂቅ አዋጁ በነባሩ አዋጅ ውስጥ የተደነገጉ ገደቦችን በተግባር ላይ ሲውሉ ይስተዋሉ የነበሩ የአተገባበር ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን ያካተተ መሆኑን የገለጸው ቋሚ ኮሚቴው አስመጪዎች በቀረጥና ታክስ አወሳሰን ላይ ያላቸውን አቤቱታ በማቅረብ ሂደት ያጋጥሟቸው የነበሩ የአሠራር መሰናክሎችን ለማስወገድ የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን ያካተተ መሆኑንም ጠቁሟል።
የምክር ቤት አባላት በኮንትሮባንድ ጭነት ምክንያት ተሽከርካሪ እንዲወረስ የሚያስችል ድንጋጌ ቢኖርም፣ ባለቤቱ በድርጊቱ ተሳታፊ ባልሆነበት ሁኔታ ንብረቱ ሊወረስ እንደማይገባም አንስተዋል።
ባለቤቱ ተሽከርካሪውን አሽከርካሪ እንዲጠቀምበት በውል ሲያስረክብ፣ ታማኝና ለሕግ ተገዥ የሆነ ሹፌር መቅጠር እንዲሁም ለሚደርስ ጉዳት ወይም ሕገ-ወጥ ድርጊት ተገቢ ዋስትና መውሰድ እንዳለበት በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።
በመጨረሻም ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ፣ የጉምሩክ አዋጅን እንደገና ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በሁለት ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል፡፡
#EBS
#EBSTVNEWS
#EBSTVSPORT
#_7696_WN
https://t.me/ebstvnews
