News

አዲስ ነገር – ሳዑዲ አረቢያ እና ኢራን ኢምባሲዎቻቸውን መልሰው ለመክፈት ከስምምነት መድረሳቸው ተሰማ፡፡

🇮🇷#ኢራን
ሳዑዲ አረቢያ እና ኢራን በየአገሮቻቸው ያሉ ኢምባሲዎቻቸውን መልሰው ለመክፈት ከስምምነት መድረሳቸው ተሰማ፡፡
በቻይና አሸማጋይነት የዛሬ ወር ሁለቱ ሀገራት ከመግባባት መድረሳቸውን ተከትሎ የሀገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከ7 አመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በቻይናዋ መዲና ቤጂንግ ተገናኝተው ኤምባሲዎቻቸውን ለመክፈት መስማማታቸው ነው የተገለፀው፡፡
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ የቴህራን እና የሪያድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የቀጥታ የአየር በረራ እና የንግድ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከመግባባት ደርሰዋል ይላል፡፡
በቻይና አደራዳሪነት የተወያዩት የሀገራቱ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ከዚህ ቀደም ያሏቸውን የከረሩ የሚባሉ ፖለቲካዊ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት ከስምምነት ደርሰዋል ሲል ሲኤንኤን ዘግቧል።
🇩🇪#ጀርመን
የጀርመን የጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያዎች በቀጠለው የዩክሬን ጦርነት ምክንያት ትርፋማ እየሆኑ መምጣታቸው ተነገረ፡፡
የጦር መሣሪያ አምራቾቹ በጦርነቱ ምክንያት ሽያጫቸው እና ትርፋማነታቸው በእጅጉ ሲጨምር ይህም ጀርመን በአውሮፓውያኑ 2022 ከዓለም ግዙፍ የጦር መሳሪያ ሻጭ አገራት ዝርዝር ውስጥ በ6ኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ አግዟታል ነው የተባለው፡፡
ጀርመን በአውሮፓውያኑ 2022 ብቻ 9.13 ቢሊየን ዶላር የሚገመቱ የጦር መሳሪያዎችን ለበርካታ አገራት መቸብቸቧን የዘገበው አር ቲ ነው።
ዩክሬን 2.4 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎችን ከጀርመን በመግዛት ዋነኛዋ የጀርመን የጦር መሳሪያዎች ሸማች አገር መሆኗም በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
🇸🇩#ሱዳን
በሱዳን ወታደራዊ መንግስት እና በፖሊቲካ ፓርቲዎች የታቀደው የሲቪል የሽግግር መንግስት የምስረታ ሰነድ ፊርማ በድጋሚ መራዘሙ ተሰምቷል።
የሱዳን ወታደራዊ መሪዎች እና የአገሪቱ የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ሃይል መካከል አለመግባባት መፈጠሩን ተከትሎ በዛሬው እለት ሊካሄድ የታቀደው የሲቪል የሽግግር መንግስት ምስረታ የሰነድ ፊርማ ለሁለተኛ ጊዜ መራዘሙ ነው የተሰማው።
በእንግሊዝኛው ምህጻሩ “ኤፍ ዲ ኤፍ ሲ” የተባለው የፖለቲካ ፓርቲ በዛሬው እለት የሚደረገው የሽግግር መንግስት ምስረታ ሂደት ተራዝሟል ሲል አስታውቋል።
የሱዳን ወታደራዊ መንግስት የአገሪቱ የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል ከመከላከያ ሰራዊቱ ጋር በሚዋሀድበት አግባብ ላይ ከስምምነት ባለመደረሱ ውይይት መቀጠሉን የኤፒ ዘገባ ያሳያል፡፡
🇸🇴#ሶማሊያ
ሶማሊያ እና ኩባ ለ46 አመታት ሻክሮ የቆየውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማደስ መስማማታቸው ተዘገበ፡፡
የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ኩባ ከ46 አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሶማሊያ የሾመቻቸውን አምባሳደር ጂዋን ማኑኤልን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል ።
የሶማሊያው የቀድሞ መሪ ሲያድ ባሬ በአውሮፓውያኑ 1977 በኢትዮጵያ ላይ የከፈተውን ጦርነት ተከትሎ ኩባ ለኢትዮጵያ ወታደራዊና የቴክኒክ ድጋፍ ማድረጓን ተከትሎ ሶማሊያ እና ኩባ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ላለፉት 46 አመታት አቋርጠው መቆየታቸው ተነግሯል፡፡
በሶማሊያ የኩባ አዲሱ አምባሳደር ጂዋን ማኑኤል የሁለቱን አገራት የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር ይሰራል ማለታቸውን ዘ ኢስት አፍሪካን ዘግቧል።

ዘወትር ከሰኞ እስከ ዓርብ

👉 የማለዳ ዜና ከጠዋቱ 1:30 ሰዓት እስከ 2:00 / በድጋሚ ከ ጠዋቱ 3፡00 እስከ 3፡30

👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:30 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት (በቀጥታ)

👉 የምሽት ዜና ከምሽቱ 1:30 እስከ 2:00

ዘወትር ቅዳሜ

👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:00 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት

ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ዜናዎች በፍጥነት እና በየእለቱ ይዘገቡበታል።

አዲስ ነገር / What’s New