News

አዲስ ነገር – ኬንያ ለመጀመሪያ ጊዜ የቅኝት ሳተላይቷን ወደ ጠፈር ልታመጥቅ እንደሆነ ተሰምቷል።

🇰🇪#ኬንያ
ጎረቤት አገር ኬንያ ለመጀመሪያ ጊዜ የቅኝት ሳተላይቷን በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ጠፈር ልታመጥቅ እንደሆነ ተሰምቷል።
“ታይፋ1” የተባለችው የቅኝት ሳተላይቷ በኬንያውያን መሃንዲሶች የተሰራች መሆኑ ሲነገር በአሜሪካው የስፔስ ኤክስ ኩባንያ በኩል ከአሜሪካ ካሊፎርኒያ የጠፈር ጣቢያ በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ጠፈር ታመጥቃለች ተብሏል ።
የኬንያ የመከላከያ ሚኒስቴር እና የኬንያ የጠፈር ኤጀንሲ በሚቀጥለው ሳምንት የምትመጥቀው የቅኝት ሳተላይት ገና በጅምር ደረጃ ላለው የአገሪቱ የጠፈር ምርምር ታላቅ እመርታን ያመጣል ሲሉ በጋራ ባወጡት መግለጫ ይፋ አድርገዋል፡፡
የኬንያዋ የቅኝት ሳተላይት በግብርና እና በምግብ ደህንነት ዙሪያ ጠቃሚ መረጃዎችን ከጠፈር ለማሰባሰብ የጐላ ጠቀሜታ አለው መባሉን አልጀዚራ ዘግቧል።

🇺🇸#አሜሪካ
አሜሪካ በጥብቅ ስትፈልገው የነበረውን የአሸባሪውን አይ ኤስ ኤስ አንድ ከፍተኛ መሪ ገድያለሁ አለች፡፡
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በአውሮፓ በርካታ የሽብር ጥቃቶችን ሲያቀነባብር የነበረውን የአሸባሪው የአይ ኤስ ኤስ መሪ ካህሊድ አይድ አህመድ ላይ በተፈፀመ የአየር ጥቃት በሶርያ መገደሉን ነው ይፋ ያደረገው፡፡
የአሜሪካ መንግስት በአሸባሪው ካህሊድ አይድ አህመድ ላይ የወደሰድኩት እርምጃ የአሸባሪው አይኤስ ኤስ ሽብር የመፈጸም አቅሙን የሚያዳክም ነው ማለቱን ቢቢሲ ዘግቧል ።
🇸🇴#ሶማሊያ
የመንግስታቱ ድርጅት በሶማሊያ በደረሰው ከባድ የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ በትንሹ 21 ሰዎች መሞታቸውን አስታወቀ፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት (ኦቻ) በሶማሊያ ላለፉት ሁለት ሳምንታት በደረሰው የጐርፍ አደጋ በትንሹ 21 ሰዎች ለህልፈት ሲዳረጉ ከ1ዐዐ ሺ የሚበልጡ ሰዎች ተፈናቅለዋል ብሏል፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት በጐርፍ አደጋው በደቡባዊ ሶማሊያ የሚገኘው በርዲር አካባቢ መጎዳቱን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በሶማሊያ የደረሰው ይሄው የጐርፍ መጥለቅለቅ አደጋ ያጋጠመው በአገሪቱ ከ 8.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ በሚፈልጉበት ጊዜ መሆኑን ሲጂቲኤን ዘግቧል ።
🇨🇬#ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ
በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምስራቃዊው የአገሪቱ ክፍል ባጋጠመው የመሬት መንሸራተት አደጋ በትንሹ 21 ሰዎች መሞታቸው ተነገረ፡፡
በዴሞክራቲክ ኮንጎ ምስራቃዊው ክፍል በደረሰው ከባድ የመሬት መንሸራተት አደጋ በትንሹ 21 ሰዎች ሲሞቱ ሌሎች በርካቶች የደረሱበት እንደማይታወቅ የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
በዴሞክራቲክ ኮንጎ የነፍስ አድን ሰራተኞች ባደረጉት ጥረት 13 ህጻናትን እና 8 ሴቶችን ከመሬት ፍርስራሹ ሥር መታደጋቸውን አልጀዚራ በዘገባው አስነብቧል፡፡

ዘወትር ከሰኞ እስከ ዓርብ

👉 የማለዳ ዜና ከጠዋቱ 1:30 ሰዓት እስከ 2:00 / በድጋሚ ከ ጠዋቱ 3፡00 እስከ 3፡30

👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:30 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት (በቀጥታ)

👉 የምሽት ዜና ከምሽቱ 1:30 እስከ 2:00

ዘወትር ቅዳሜ

👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:00 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት

ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ዜናዎች በፍጥነት እና በየእለቱ ይዘገቡበታል።

አዲስ ነገር / What’s New