News

አዲስ ነገር – ዜለንስኪ የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂን ፒንግ ዩክሬንን እንዲጎበኙ መጋበዛቸው ተሰማ፡፡

🇺🇦#ዩክሬን
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂን ፒንግ ዩክሬንን እንዲጎበኙ መጋበዛቸው ተሰማ፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ከኤፒ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ከቻይናው መሪ ጋር አለመገናኘታቸውን ገልጸው ፕሬዚዳንት ሺ ጂን ፒንግ ዩክሬንን እንዲጎበኙ ጋብዣቸዋለሁ ብለዋል፡፡
ቻይና የዩክሬን ጦርነት እንዲቆም ባለ 12 ነጥብ የሰላም ፍኖተ ካርታ ከአንድ ወር በፊት ይፋ ማድረጓ ይታወሳል፡፡
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይዋ ማኦ ኒንግ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ለቻይናው መሪ ያቀረቡትን የጉብኝት ጥያቄ በተመለከተ መረጃ እንደሌላቸው አርቲ በዘገባው ዳሶታል።
🇹🇷#ቱርክ
የቱርኩ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶሃን ምዕራባዊያን ቱርክ ከሩሲያ ጋር ወደ ግጭት እንድትገባ እየገፋፉ ነው ሲሉ ከሰሱ፡፡
ፕሬዚዳንት ኤርዶሃን ምንም እንኳን ምዕራባዊያኑ ከሩሲያ ጋር እንድንጋጭ በአደገኛ ሁኔታ ቢገፋፉም በእኛ ጥንካሬ አላማቸው መና ቀርቷል ሲሉ ተናግረዋል ።
ፕሬዚዳንቱ የአንካራ መንግስት እንደዚህ ቀደሙ ሁሉ ሩሲያ እና ዩክሬን ወደ ንግግር እንዲመለሱ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይገፋበታል ማለታቸውን አር ቲ ዘግቧል።
ቱርክ እህል ከዩክሬን እንዲወጣ የተደረሰውን ዓለም አቀፍ ስምምነት እንዲፈረም ስኬታማ ሚና መጫወቷ በዘገባው ተጠቁሟል።
🇸🇸#ደቡብ ሱዳን
የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ከተደረሰው የሰላም ስምምነት ውጪ አዲስ የመከላከያ ሚኒስትር መሾማቸው ተነገረ፡፡
ፕሬዚዳንት ኪር በአውሮፓውያን 2018 የተደረሰውን የሰላም ስምምነት በመጣስ ነው ከራሳቸው ፓርቲ አንዱ የሆኑትን አመራር የመከላከያ ሚኒስትር አድርገው መሾማቸው የተነገረው፡፡
በአውሮፓውያኑ 2018 በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሰረት የመከላከያ ሚኒስትርን የሚሾመው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው እና የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር እንደሆኑ ዘኢስት አፍሪካን ዘግቧል ።
ከአመታት በፊት በተካሄደው የደቡብ ሱዳኑ ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት 4መቶ ሺ የአገሪቱ ዜጐች መገደላቸው በዘገባው ለትውስታ ቀርቧል ::
🇺🇸#አሜሪካ
የሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም በምህጻ ቃሉ “ኤ.አይ” በመላው ዓለም የ 3 መቶ ሚሊየን ሰራተኞችን ስራ ሊነጥቅ እንደሚችል አንድ ሪፖርት አመለከተ ።
የአሜሪካው የጐልድማን ሳክስ ባንክ የሰው ሰራሽ አስተውሎት በዓለም ላይ 3 መቶ ሚሊየን ሰራተኞችን ከሥራ ሊያፈናቅል እንደሚችል ባወጣው ሪፖርቱ አስታውቋል ።
ባንኩ በአሜሪካ እና አውሮፓ 60 ከመቶ የሚጠጉ ሥራዎች በሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም ሊተኩ ከመቻላቸው ጋር በተያያዘ ዜጐች አደጋ ተደቅኖባቸዋል፡፡
የሰው ሰራሽ አስተውሎት ኤ አይ ቴክኖሎጂ አካል የሆነው አነጋጋሪው “ቻት ጂፒቲ ” ሰውን ተክቶ የፅሁፍ ሥራዎችን የሚሰራ መሆኑ በዘገባው ተጠቅሷል።

ዘወትር ከሰኞ እስከ ዓርብ

👉 የማለዳ ዜና ከጠዋቱ 1:30 ሰዓት እስከ 2:00 / በድጋሚ ከ ጠዋቱ 3፡00 እስከ 3፡30

👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:30 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት (በቀጥታ)

👉 የምሽት ዜና ከምሽቱ 1:30 እስከ 2:00

ዘወትር ቅዳሜ

👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:00 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት

ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ዜናዎች በፍጥነት እና በየእለቱ ይዘገቡበታል።

አዲስ ነገር / What’s New