News

አዲስ ነገር – ቻይና የታይዋን ፕሬዚዳንት በአሜሪካ ሊያካሂዱ ያሉትን ጉብኝት ተከትሎ ታይዋንን አስጠነቀቀች

🇨🇳#ቻይና
ቻይና የታይዋን ፕሬዚዳንት በአሜሪካ ሊያካሂዱ ያሉትን ጉብኝት ተከትሎ ታይዋንን አስጠነቀቀች።
የታይዋኑ ፕሬዚዳንት በአሜሪካ ጉብኝታቸው በተለይ ከአሜሪካ ኮንግረስ አፈጉባኤ ኬቨን ማካርቲ ጋር ተገናኝተው የሚመክሩ ከሆነ የቤጂንግ መንግስት በታይዋን ላይ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ማስጠንቀቁ ነው የተነገረው።
የታይዋኑ ፕሬዚዳንት ሳይ ኢንግ ዌን በአሜሪካ ከዛሬ ጀምሮ ለ10 ቀናት የሥራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የአገሪቱ የፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት ማስታወቁን አር ቲ ዘግቧል ።
የቻይና መንግስት አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን የታይዋኑ ፕሬዚዳንት ሳይኢንግ ዌን የአሜሪካ ጉብኝት የቻይናን ሉአላዊነት የሚጋፋ እና ፀብ አጫሪ ነው ሲሉ ኮንነዋል ::
የአሜሪካ ኮንግረስ የቀድሞ አፈጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ በአውሮፓውያኑ 2022 በታይዋን ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ቻይና ግዙፍ የተባለ የባሕር ኃይል ወታደራዊ ልምምድ በታይዋን አቅራቢያ ማካሄዷ በዘገባው ተመልክቷል።
🇺🇸#አሜሪካ
በአሜሪካ እየተበራከተ ከመጣው የጦር መሣሪያ ወንጀል ጋር በተያያዘ በ3 ወራት ውስጥ ብቻ 10ሺ ሰዎች መገደላቸው ተሰምቷል።
በሀገሪቱ በተያዘው የአውሮፓውያኑ 2023 ያለፉት 3 ወራት ውስጥ 130 የጅምላ ግድያዎች ሲመዘገቡ 10ሺ ንፁሃን ዜጎች በጅምላ ግድያዎቹ ህይወታቸውን አጥተዋል ተብሏል፡፡
“ገን ቫየለንስ አርካይቭ” የተባለው የመረጃ ተቋም ባወጣው ሪፖርቱ ባለፉት 3 ወራት በአሜሪካ በጅምላ ግድያ ሳቢያ በየእለቱ 111 አሜሪካውያን ተገድለዋል ።
ቲአርቲ ወርልድ የተቋሙን መረጃ ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው በጅምላ ግድያው ከሞቱት በተጨማሪ 7500 የሚበልጡ ሰዎች የከፋ ጉዳት ደርሶባቸዋል ።
🇷🇺#ሩሲያ
ሩሲያ የኒውክለር የጦር መሣሪያዎችን በተመለከተ ከአሜሪካ ጋር ስታካሂደው የነበረውን የመረጃ ልውውጥ ትብብር ማቋረጧን ይፋ አደረገች ።
የሩሲያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ራይባኮቭ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ሞስኮ የኒውክለር የጦር መሳሪያዎችን እና የሚሳኤል የሙከራ ጉዳይ በተመለከተ ከአሜሪካ ጋር የሚደረገው የመረጃ ልውውጥ መቋረጡን ነው ያብራሩት፡፡
ሀገሪቱ የባይደን አስተዳደር በኒውክለር መርሃ ግብሬ ላይ አንዳች ቁጥጥር እንዲያካሂድ አልፈቅድም በሚል ምክንያት “ስታርት” ከተባለው ዓለም አቀፍ የኒውክለር ስምምነት ከወራት በፊት በጊዜዊነት መውጣቷ ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩሲያ በሳይቤሪያ ግዛት አዲስ ግዙፍ ወታደራዊ ልምምድ እያደረገች መሆኑን ኤፒ ዘግቧል።
#አውሮፓ ሕብረት
አሜሪካ ለአውሮፓ ሕብረት አገራት ግንባር ቀደም የነዳጅ ዘይት ምርቶች አቅራቢ አገር መሆን መቻሏን አንድ ሪፖርት አመለከተ፡፡
እንደ ዩሮ ስታት መረጃ አሜሪካ ሩሲያን በልጣ ለሕብረቱ ሀገራት ቁጥር 1 የነዳጅ ዘይት አቅራቢ አገር መሆን መቻሏ ነው የተነገረው ።
በሩሲያ ላይ በተጣለው ማዕቀብ ሳቢያ ሩሲያ ወደ አውሮፓ የምትልከው አምና 31 ከመቶ ከነበረው ዘንድሮ ወደ 4 ከመቶ ሲቀንስ በአንፃሩ አሜሪካ ለአውሮፓ ሕብረት የምታቀርበው የነዳጅ ዘይት ምርት ከአምናው አንጻር ዘንድሮ በ18 ከመቶ ማደጉ ተዘግቧል፡፡
ሩሲያ በበኩሏ ወዳጅ አይደሉም ላላቻቸው ሀገራት የሚላከውን የነዳጅ ዘይት ምርት አቁማ ለእስያ ፣ አፍሪካ፣ ላቲን አሜሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የነዳጅ ምርቶቿን እየላከች መሆኑን አር ቲ ዘግቧል።

ዘወትር ከሰኞ እስከ ዓርብ

👉 የማለዳ ዜና ከጠዋቱ 1:30 ሰዓት እስከ 2:00 / በድጋሚ ከ ጠዋቱ 3፡00 እስከ 3፡30

👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:30 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት (በቀጥታ)

👉 የምሽት ዜና ከምሽቱ 1:30 እስከ 2:00

ዘወትር ቅዳሜ

👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:00 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት

ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ዜናዎች በፍጥነት እና በየእለቱ ይዘገቡበታል።

አዲስ ነገር / What’s New