አዲስ ነገር – አጫጭር የዓለም መረጃዎች
🇮🇱#እስራኤል
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታናያሁ የአገሪቱን የመከላከያ ሚኒስትር ከስልጣን ማሰናበታቸውን ተከትሎ በአገሪቱ ተቃውሞ ተባብሶ መቀጠሉ ተሰማ።
በእስራኤል መዲና ቴላቪቭ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታናያሁ የአገሪቱን የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንትን ከስልጣን ማሰናበታቸውን በመቃወም ሰልፍ አካሂደዋል ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታናያሁ በአገሪቱ ፍ/ቤቶች ላይ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ የያዙትን እቅድ የመከላከያ ሚኒስትሩ በመቃወማቸው ከስልጣን እንደተባረሩ ቪኦኤ ዘግቧል።
በእስራኤል 800ሺ ሰራተኞችን የሚወክሉ ልዩ ልዩ የሰራተኛ ማኅበራት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔ በመቃወም የስራ ማቆም አድማ መተው መዋላቸውን ኤፒ ዘግቧል ።
🇸🇦#ሳዑዲ አረቢያ
የሳዑዲ አረቢያ እና የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በአካል ተገናኝተው ለመምከር ለመጀመሪያ ጊዜ ከስምምነት መድረሳቸው ተነገረ።
የሪያድ እና የቴህራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሚቀጥሉት 28 ቀናት ውስጥ ተገናኝተው የሚመክሩት በቅርቡ የተፈራረሙትን ታሪካዊውን የሰላም ስምምነት ገቢራዊ ለማድረግ መሆኑ ነው የተዘገበው።
የሳዑዲ አረቢያ የዜና ወኪል የቴህራን እና የሪያድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ለሁለተኛ ጊዜ በስልክ መወያየታቸውን የሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከ7 አመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊገናኙ እንደሆነ የዘገበው አልጀዚራ ነው ::
🇺🇸#አሜሪካ
የአሜሪካዋ ምክትል ፕሬዝዳንት ካምላ ሀሪስ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን በጋና ጀምረዋል ተባለ።
ምክትል ፕሬዝዳንት ካምላ ሀሪስ በጋና ጉብኝታቸው የምዕራብ አፍሪካ ቀጠና ሰላም በሚረጋገጥበት ዙርያ ከጋና ባለስልጣናት ጋር እንደሚወያዩ እና ለጋና የ139 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ይፋ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
ምክትል ፕሬዚዳንቷ ሀሪስ በተለይ የጋና ምጣኔ ሀብት እንዲያድግ በሚረዱ ጉዳዮች ላይ አፅንኦት ሰጥተው ከአክራ ባለስልጣናት ጋር ይወያያሉ ተብሏል።
ፕሬዚዳንቷ በአፍሪካ የሚያደርጉትን ጉብኝት ቀጥለው በታንዛኒያ እና ዛምቢያ ሀገራት የሥራ ጉብኝት ያደርጋሉ ሲል ዩፒአይ ዘግቧል።
🇰🇪#ኬንያ
በጎረቤት አገር ኬንያ ለሁለተኛ ጊዜ የተጠራውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የአገሪቱ ፖሊስ በተጠንቀቅ ላይ መሆኑ ተሰማ፡፡
የኬንያ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ራይላ ኦዲንጋ ኬንያውያን በአደባባይ ወጥተው ተቃውሞ ማሰማት መብታቸው ነው ሲሉ ጥሪ ቢያቀርቡም የአገሪቱ ፖሊስ አዛዥ ጃፌዝ ኩም ለዛሬ የተጠራው የተቃውሞ ሰልፍ በመንግስት ተቀባይነት የሌለው ህገ ወጥ ድርጊት ነው ሲሉ ተናግረዋል ።
ተቃውሞ አድራጊዎቹ ኬንያውያን ኑሮ ተወዶብናል በሚል ምሬታቸውን ገልጸው የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ስልጣን እንዲለቁ ጭምር ጥያቄ አቅርበዋል።
በኬንያ በርካታ የሲቪል ማኅበራት የኬንያ መንግስት ተቃውሞውን ህገ ወጥ ነው በሚል የህዝብን ድምፅ ለማፈን እያደረገው ያለው ጥረት አሳሳቢ ነው ሲሉ ስጋታቸውን እንደገለፁ ኤፒ ዘግቧል።
ዘወትር ከሰኞ እስከ ዓርብ
👉 የማለዳ ዜና ከጠዋቱ 1:30 ሰዓት እስከ 2:00 / በድጋሚ ከ ጠዋቱ 3፡00 እስከ 3፡30
👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:30 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት (በቀጥታ)
👉 የምሽት ዜና ከምሽቱ 1:30 እስከ 2:00
ዘወትር ቅዳሜ
👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:00 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት
ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ዜናዎች በፍጥነት እና በየእለቱ ይዘገቡበታል።
አዲስ ነገር / What’s New