News

አዲስ ነገር – የሱዳን የፖለቲካ ፓርቲዎች የሽግግር መንግስት ምስረታ

🇸🇩#ሱዳን
የሱዳን የፖለቲካ ፓርቲዎች የሽግግር መንግስት ምስረታ ለማካሄድ ከስምምነት መድረሳቸው ተዘገበ።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ቃለ አቀባይ ካህሊድ ኦማር ዩሱፍ የሱዳን የሽግግር መንግስት ምስረታው በአውሮፓውያኑ ኤፕሪል 11 እንዲደረግ ከስምምነት መደረሱን ነው ይፋ ያደረጉት።
አዲስ የሚመሰረተው የሱዳን የሽግግር መንግስት 9 የፖለቲካ ፓርቲዎች ፣ የአገሪቱ ጦር እና የሱዳን የሚሊሻ ሰራዊት ወይም “አርኤስ ኤፍ”ን ያካተተ መሆኑን ቃለ አቀባዩ ለሮይተርስ ተናግረዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በሱዳን አዲስ ህገ መንግሥት ለማርቀቅ ጭምር ከስምምነት መድረሳቸው በዘገባው ተጠቅሷል።

🇨🇳#ቻይና
የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂን ፒንግ ታሪካዊ ነው የተባለውን የሩሲያ ጉብኝት ለማድረግ ሞስኮ መግባታቸው ተሰምቷል፡፡
የቻይናው ፕሬዚዳንት ለ3 ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በሩሲያ መዲና ሞስኮ መግባታቸው ሲነገር ጉብኝታቸው “ገደብ የለሽ” የተባለውን የሃገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል ተብሏል።
የክሬምሊን ቃለ አቀባይ ዲምትሪ ፔስኮቭ የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂን ፒንግ ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር በዩክሬን ጦርነት እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ በጥልቀት ይመክራሉ ብለዋል።
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የቻይናው መሪ በሩሲያ የጀመሩት ጉብኝት የሁለቱን አገራት ልዩ ወዳጅነት ማሳያ ነው ሲሉ ለቻይና መገናኛ ብዙሃን መናገራቸውን ኤፒ ዘግቧል።

🇮🇷#ኢራን
የኢራኑ ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራይሲ በሳዑዲ አረቢያ ጉብኝት እንዲያደርጉ ከሳዑዲ አረቢያ መንግስት ግብዣ እንደቀረበላቸው ኢራን አስታወቀች፡፡
የሳዑዲ አረቢያው ንጉስ ሰልማን ለኢራኑ ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራይሲ በሃገራቸው የሥራ ጉብኝት እንዲያደርጉ ለቴህራን መንግስት ደብዳቤ መላካቸው ነው የተዘገበው ።
የሳዑዲ አረቢያ የጉዞ ግብዣ የቀረበው ባላንጣዎቹን ኢራን እና ሳዑዲ አረቢያ የሻከረ ግንኙነታቸውን መልሰው ለማሻሻል በቻይና አሽማጋይነት መስማማታቸው በተገለፀ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሚር አብዶላህያን ለመገናኛ ብዙኀን በሰጡት መግለጫ ሪያድ እና ቴህራን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ ስብሰባ ለማካሄድ ተስማምተዋል ብለዋል።

🇾🇪#የመን
የየመን መንግስት እና የሃውቲ አማፅያን የእስረኞች ቅይይር ለማድረግ ከስምምነት መድረሳቸው ተገለፀ ።
በመንግስታቱ ድርጅት እና በዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ አሸማጋይነት በስዊዘርላንድ የተካሄደውን ውይይት ተከትሎ የየመን መንግስት እና የሃውቲ አማፅያን 880 እስረኞችን ለመቀያየር ተስማምተዋል።
የየመን መንግስት 706 እስረኞችን ለመልቀቅ እና የሃውቲ አማፅያን በፊናቸው 181 የመንግስት እስረኞችን ነጻ ለማድረግ ከስምምነት መድረሳቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የመንግስታቱ ድርጅት አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን ለፀጥታው ምክር ቤት በሰጡት ምስክርነት በየመን የቀጠለው ጦርነት እንዲቆም እና የሰላም ስምምነት እንዲደረስ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እየተካሄደ ነው ብለዋል።

ዘወትር ከሰኞ እስከ ዓርብ

👉 የማለዳ ዜና ከጠዋቱ 1:30 ሰዓት እስከ 2:00 / በድጋሚ ከ ጠዋቱ 3፡00 እስከ 3፡30

👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:30 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት (በቀጥታ)

👉 የምሽት ዜና ከምሽቱ 1:30 እስከ 2:00

ዘወትር ቅዳሜ

👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:00 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት

ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ዜናዎች በፍጥነት እና በየእለቱ ይዘገቡበታል።

አዲስ ነገር / What’s New